የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ወደ ቀድሞው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ ነው—የክልሉ መንግስት

465

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2012(ኢዜአ) በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም የነበረው የሰላም እጦት በአንጻሩ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ መደርሳ ለኢዜአ እንዳሉት ከዚህ ቀደም የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በአካባቢው ችግር ሲፈጥር ቆይቷል።

ሆኖም መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ባደረገው እንቅስቃሴ ታጣቂ ኃይሉን ለመቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያና በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ሰላም “አስተማማኝ” ሊባል የሚችል ሁኔታ ላይ ይገኛ ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነር ጀነራል አራርሳ ገለጻ የአካባቢው ህብረተሰብ ከመንግስት የጸጥታ አካል ጋር በመሆን የራሱን ሰላም በራሱ እየጠበቀ ይገኛል፡፡

እንደ ከዚህ ቀደሙ “በዘፈቀደ ሰው የሚገደልበትና ህብረተሰቡም የስጋት ኑሮ የሚመራበት ሁኔታ አሁን የለም” ብለዋል ኮሚሽነሩ።

የኦሮሚያ ክልል ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በበኩሉላቸው በአካባቢው የልማት ሥራዎችና ማህበራዊ አገልግሎት ወደ ቀድሞው ሰላማዊ ሁኔታ ተመልሰዋል ብለዋል።

የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

ይሁንና በቅርቡ መንግስት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል ነው ያሉት።  

በምእራብ ኦሮሚያ አካባቢ ታጥቆ ጫካ የሚንቀሳቀሰውን ሃይል ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን ያደረገ ቢሆንም ምላሽ አለመኖሩን አቶ ጌታቸው አስረድተዋል።

ሆኖም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል በአካባቢው በሚንቀሳቀሰው ታጣቂሃይል ላይ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ገልጸዋል።