ለኮሮናቫይረስ ምርመራ የሚያገለግሉ 2 ተጨማሪ ላብራቶሪዎች ሊከፈቱ ነው

65

አዲስ አዲስ መጋቢት 16/2012 (ኢዜአ) ለኮሮናቫይረስ (ኮቪድ -19) ምርመራ የሚያገለግሉ ሁለት ተጨማሪ ላብራቶሪዎች ሊከፈቱ መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ።

የቫይረሱን በፍጥነት የመስፋፋት ባህሪ ከግምት በማስገባት የመመርመሪያ መሳሪያ ባላቸው ተቋማት ላይ ተጨማሪ ላቡራቶሪ አንዲኖር ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ቢሾፍቱ አካባቢ የሚገኝ ናዲክ የተባለ የግብርና ምርምር ተቋምና አርማዎር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲቲዩት ወደ ስራ ለመግባት ዝግጁ ሆነዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በደም ውስጥ የሚኖርን የኤች አይቪ ቫይረስ መጠን ለማወቅ የሚያገለግለው መሳሪያ ኮቪድ-19 ቫይረስን የመመርመር አቅም አለው ብለዋል።

መሳሪያው በሁሉም ክልሎች በሚገኙ 19 ተቋማት ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ መሳሪያዎች ለኮሮናቫይረስ መመርመሪያ የራሳቸው የሆነ ኪት ስለሚያስፈልጋቸው ከአምራች ካምፓኒዎቹ ተገዝቶ እንዲቀርብ ግዥ መቅረቡንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከውጭ ለጋሽ ደርጅቶች የተገኙ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ጨምሮ በአገር ውስጥ የሚገኙት በሙሉ ዝግጁ ሲሆኑ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።

በየክልሎቹ የመመርመሪያ ጣቢያ እንዲኖርና ምርመራውን በስፋት እንዲካሄድ የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ዝግጅት አንድዳንድ ክልሎች ጥሩ ዝግጅት እያደረጉ ቢሆንም ወደ ኋላ የቀሩ እንዳሉም ዶክተር ኤባ ገልፀዋል።

በመሆኑም የክልሎችን እንቅስቃሴ የሚደግፍ በፌደራል መንግስት የተዋቀረ ቡድን ከነገ ጀምሮ ወደ ክልሎቹ ተሰማርቶ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል።

በኢትይጵያ እስካሁን 576 ሰዎች ላይ የላዓብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 555ቱ ከቫይረሱ ነፃ ሲሆኑ 9ኙ ገና ውጤት እየጠበቁ ይገኛሉ።

እስካሁን ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡት ደግሞ 12 ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የጃፓን ዜጎች ወደ ሃገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።

መንግስት በ1 ሺህ 923 ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ሰዎች በስልክ ክትትል  ሲደረግላቸው ቆይቶ 1 ሺህ 772ቱ  በ14 ቀን ውስጥ ምልክት ባለማሳየታቸው ክትትሉ ተቋርጧል።

ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል የገቡ 473 ደግሞ በስካይ ላይትና በጊዮን ሆቴሎች የ14 ቀናት ቆይታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በመንግስት በኩል ሻይረሱን ከወዲሁ ለመከላከል የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉና ርምጃዎችም እየተወሰዱ መሆኑን ዶክተር ኤባ ገልጸዋል።

በማህበረሰቡ በኩል ግን በብዛት አሁንም መንግስት የሚያስተላፋቸውን ውሳኔዎችና የሃይማኖት ተቋማት የሚሰጧቸውን ማሳሰቢያዎች ተግባራዊ ሲያደርጉ አይስተዋልም።

በመሆኑም ቫይረሱ አደገኛና በፍጥነት የሚተላለፍ መሆኑን ተገንዝቦ ህዝቡ ጥንቃቄ ማድረግ አንዳለበት አሳስበዋል።

የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያም ከገባ ቀናቶች ተቆጥረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም