በአርብቶ አደሮች አካባቢ የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ እንደሚፈለገው አልተከናወነም

59

አዲስ አበባ፣መጋቢት 16/2012 (ኢዜአ) በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ በጸጥታና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች ሳቢያ በሚፈለገው መልኩ እንዳልተከናወነ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።

መርሃ ግብሩ በሚፈለገው መጠን ያልተከናወነው የሰዎች የአመለካከት ችግር፣ ከሰፈሩ በኋላ ለቆ የመሄድ፣ የጸጥታ ችግር እና መሰረተ ልማቶች በታቀደው መሰረት ባለመከናወናቸው መሆኑ ተጠቅሷል።

የመንደር ማሰባሰቡ ሂደት የአርብቶ አደሩን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳለጥ በማሰብ ነው።

ከመሆኑም ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ366 ሺህ በላይ አባወራዎች በ600 መንደሮች ማሰባሰብ መቻሉን የሰላም ሚኒስቴር ገልጿል።

በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና የልዮ ድጋፍ ዳይሬክተር ጄኔራል ፕሮፌሰር ደገፋ ቶለሳ ለኢዜአ እንደገለጹት የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ በሱማሌ፣ አፋር፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ እና ጋምቤላ ክልሎች እየተከናወነ ነው።

ሆኖም የእስካሁኑ ክንውን በተለያዩ ምክንያቶች የታሰበውን ያክል ስኬታማ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የውሃ አቅርቦት ባለመሟላቱና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ክንውኑን አስተጓጉሎታል ብለዋል።

በሌሎች የመንደር ማሰባሰብ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ግን ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ የገጠር መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተሰርቶላቸዋል።

አርብቶ አደሩ በአንድ አካባቢ በራሱ ፍቃድ በማሳባሰብና ተረጋግቶ እንዲኖር ለማድርግ የተለያዩ ስራዎች ተሰርቷል።

በቀጣይ የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ተጨማሪ ጥናቶች እየተደረጉ ሲሆን ለህብረተሰቡም ግንዛቤ የመስጠት ስራ ቀጥሏል ብለዋል።የአርብቶ አደር አካበቢዎችን በዘላቂነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ደገፋ ከወዲሁ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ለአመራሮች፣ ለአርብቶ አደሮችና አጠቃላይ ለማህበረሰቡ የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠታቸውንም አረጋግጠዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በሁሉም አካባቢዎች በአርብቶ አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ በመደረግ ላይ ነው።

የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማ በተለይ ተበታትኖ የሚኖረውን ማህበረሰብ በአንድ መንደር በማሰባሰብ የልማትና መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም