የደብረ ማርቆስ፣አርባምንጭ፣ ባህርዳርና የወለጋ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን አስመረቁ

181
ደብረ ማርቆስ አርባ ምንጭ ባህርዳር ነቀምት 23/2010 የደብረ ማርቆስ፣አርባምንጭ፣ ባህርዳርና የወለጋ  ዩኒቨርስቲዎች በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር ያሰለጠኗቸውን ከ29ሺህ 200 በላይ  ተማሪዎችን  ዛሬ አስመረቁ ። የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በወቅቱ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ለ10ኛ ጊዜ ዛሬ ካስመረቃቸው 4ሺህ 465 ተማሪዎች ውስጥ 1ሺህ 670 ዎቹ ሴቶች ናቸው ። እንዲሁም 380 በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ተመራቂዎች በመጀመሪያ ዲግሪ በ51 በሁለተኛ ዲግሪ በ41 የትምህርት አይነቶች የሰለጠኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ። የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባልና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ወልደአምላክ በእውቀት ተመራቂዎች በሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች ህዝባቸውንና ሃገራቸውን በቅንነት፣ በታታሪነትና ከአድሎ በፀዳ መንገድ እንዲያገለግሉ መልእክት አስተላልፈዋል ። ከተመራቂዎች መካከል ከባዮ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል ታደሰ አየለ በሰጠው አሰተያየት በሰለጠነበት የሙያ መስክ ህዝቡንና ሃገሩን በቅንነት በማገልገል የለውጥ አራማጅ ለመሆን ተዘጋጅቷል ። የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ እሰካሁን ከ29 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኖ እንዳስመረቀና በአሁን ሰአት 32 ሺህ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ታውቋል። በተመሳሳይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ 5ሺህ 965 ተማሪዎችን ዛሬ ባስመረቀበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጤው ዳርዛ እንደገለፁት ዩኒቨርስቲው በውሃ ሀብት ልማትና አስተዳደር ስልጠና በመስጠት በአፍሪካ ቀዳሚው ነው" "ዩኒቨርስቲው በውሃው መስክ በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል ለመሆን ያስቀመጠውን እቅድ በአግባቡ እንዲያሳካ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ተደርጓል"ብለዋል ። በሌላ በኩል ዩኒቨርስቲው በአካባቢው ባሉ እምቅ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ሀብቶች እንዲሁም እሴቶች በመጠቀም በብዝሃ ህይወት፣ በባህል ብዝሀነት፣ በንግድ ሀሳብና ፈጠራ ልማት እንዲሁም በተዘነጉ የሞቃታማ አከባቢ በሽታዎች ምርምር የልህቀት ማዕከል ለመሆን አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ። እቅዱን በአግባቡ ለመፈጸም የውሃ፣ የግብርና፣ የጤና፣ የሳይንስና የባህል ምርምር ግንባታዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው በአሁን ሰአት ቅድመ ምረቃ በ74  በድህረ ምረቃ በ96 የትምህርት አይነቶች ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ታውቋል ። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም 11 ሺህ 227 ተማሪዎችን ዛሬ ባስመረቀበት ስነ ስርአት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ ባደረጉት ንግግር "ተመራቂዎች አገሪቱ በተለየ ሁኔታ ከጫፍ ጫፍ በፍቅር በተሳሰረችበት ወቅት መመረቃችሁ ከወትሮው ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል ። ተመራቂዎች ወቅቱ የፈጠረውን የአንድነት መንፈስ በመላበስና  መንግስት ያመቻቸውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በሀገሪቱ የለውጥ ሂደት የራሳቸውን አሻራ ሊያኖሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች ውስጥ 3ሺህ 82ቱ ሴቶች ናቸው ከአጠቃላይ ተመራቂዎችም 2ሺህ 654ቱ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ  መሆናቸው ታውቋል ። በተመሳሳይ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ፣በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ከ7 ሺህ  600 በላይ  ተማሪዎችን አስመርቋል። የኦሮሚያ ክልል  ምክትል ፕሬዝዳንት  እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን  እንደተናገሩት የዘንድሮ ተመራቂዎች  ከባለፉት ዓመታት ልዩ የሚያደርጋቸው የአንድነት ፣የመደመር፣ የፍቅርና የመቻቻል መልካም እሴቶች  በመላው ኢትዮጵያ በታወጀበት  ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ ተመራቂዎች  የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች በትምህርት ቆይታቸው ካገኙት  እውቀት ጋር በማቀናጀት ለሀገሪቱ እድገትና ብልጽግና መስራት እንዳለባቸውም አሳሰበዋል፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አረባ ሚጀና በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች  በቀሰሙት ትምሀርት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው እራሳቸውን ጠቅመው የሀገራቸውን   ልማት ለማገዝ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በመደበኛ፣በተከታታይ፣በማታው መረሃግብር ነው። ኢንጂነርንግ፣ ህክምና፣በብዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ስነ ትምህርትና ስነ ባህል፣ ህግ ፣ቋንቋና ተግባቦት ተመራቂዎቹ ከሰለጠኑባቸው የትምህርት መስኮች መካከል ይገኙበታል፡፡ ከተመራቂዎች መካከል ተማሪ ጥላሁን ልጃለም በሰጡት አስተያየት “ አካል ጉዳተኝነት ዓላማን አያግድም እኔ አይነ ስውር ብሆንም  ዓላማዬ ተሳክቶልኛል “ብሏል። በተማረው የሲቪክና ስነ ዜጋ ትምህርት  አራት ነጥብ በማምጣት ከዩኒቨርሲቲው የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆኑ መደሰቱንም ተናግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም