ኩታገጠም መሰረት ያደረገው የምርምር ስራ ውጤት እየታየበት መሆኑ ተገለጸ

287

መቀሌ መጋቢት 15/2012 (ኢዜአ) ኩታገጠም መሰረት ያደረገው የግብርና ምርምር ስራ ድግግሞሽ ከማስቀረት በተጨማሪ ማእከላቱ አከባቢያቸውን መሰረት ያደረጉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲያወጡ እገዛ ማድረጉን የትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ ።
የኢንስቲትዩቱ  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እያሱ አብርሃ  ለኢዜአ እንደገለጹት ክልሉ የአካባቢ ምህዳርን መሰረት ባደረገ በስድስት  የምርምር ማእከላት ተዋቅሯል።

ኩታ ገጠም የምርምር ስራ የምርምር ድግግሞሽን ከማስቀረቱ በተጨማሪ በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት በሚገባ እንዲፈተሽ ያደርጋል ብለዋል።

ማእከላቱ በአዝርእት ልማት የሰሊጥ፣የማሽላ፣የስንዴና የጤፍ የተሻሻሉ  ዝርያዎችን  ለማውጣት መቻላቸውን  አስረድተዋል።

የሰቲት ሑመራ ግብርና ምርምር ማእከል  ባለፉት ዓመታት ሰቲት አንድ፣ ሰቲት ሁለት፣  ሰቲት ሶስት የተባሉ አዳዲስ ዝሪያዎን በማፍለቅ የሰሊጥ ምርታማነት  በሄክታር ከ8 ኩንታል ወደ 16 ኩንታል ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የምርምር ግኝቱ  በአርሶ አደሮችና ባለሃብቶች የማስታዋወቅ ስራ እየተካሄደ  መሆኑንም  ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

ማሽላ አብቃይ በሆነው ሰሜናዊና ምእራባዊ ትግራይ ዞኖች ደግሞ  የማሽላ ምርታማነትን በሄክታር ከ30 ኩንታል   ወደ 45 ኩንታል ከፍ የሚያደርጉ  የተሻሻሉ ዝርያዎች መለቃቃቸውን ተናግረዋል።

የመቐለና የአላማጣ ምርምር ማእከላትም ድርቅን የሚቋቋምና በ90 ቀናት ውስጥ ለምርት የሚደርሱ የተሻሻሉ አራት ዓይነት የዳቦ ስንዴ ዝርያዎችን በመለቀቅ በአርሶ አደሩ እጅ መድረሳቸውን ዶክተር እያሱ አስረድተዋል።

ከአሁን ቀደም የነበሩ የስንዴ ዝርያዎች ከ130 ቀናት በላይ ለምርት የሚደርሱ በመሆናቸው ለድርቅ ይጋለጡ እንደነበር ገልፀዋል ።

ከአንድ  ሄክታር መሬት 17 ኩንታል ይገኝ የነበረውን የጤፍ ምርት በምርምር  በተገኙ የተሻሻሉ ዝርያዎች  ወደ 24 ኩንታል ከፍ ማድረግ መቻሉንም ዋና ዳሬክተሩ ተናግረዋል።

በእንስሳት ሃብት ደግሞ በክልሉ በጋይት ተብለው የሚታወቁ የከብት፣ የፍየልና የበግ ዝርያዎችና በንብ ማነብ  ላይ ትኩረት በማድረግ የምርምር ስራዎች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።

በክልሉ ‘’ በጋይት’’ ተብለው የሚጠሩ ከብት፣ፍየልና በግ  ዝርያዎች ከጥፋት የመጠበቅና የማራባት ስራ እየተካሄደ መሆኑን ዋና ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

”በጋይት” ከሌሎች የቤት እንስሳት ዝርያዎች ለየት የሚያደርጋቸው ጉልበታቸው ግዙፍ ከመሆኑ በተጨማሪ በተለይ የበግ ዝርያ እስከ አራት መንትያ የመውለድ አቅም አላቸው ።

በትግራይ ማእከላዊ ዞን በቆላ ተምቤን በማር በኩታ ገጠም የምርምር ስራ ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር  መዓዛ ገብረመድህን በምርምር ማእከሉ የተሰጣቸው ከሸንበቆ የተሰራ የንብ ቀፎ ከባህላዊ ቆፎ  በክበደቱና በቆይታ ጊዜው የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰቲት ሑመራ ህብረት ስራ ማህበር ዩኔየን ሊቀመንበር አቶ አምባዬ ገብረ በበኩላቸው ዩኒየኑ ከምርምር የወጡ የሰሊጥ ዝርያዎች በአርሶ አደሮች እጅ እንዲደርስና አገልግሎት ላይ እንዲውል ትምህርት ከመስጠት ባሻገር  ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።