የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስትያናት ኀብረት ህዝብ የሚሰበሰብባቸው አምልኮዎች እንዲቋረጡ አሳሰበ

108

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተክርስትያናት ኀብረት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከመንግስት የተለየ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ ሃይማኖታዊ ኮንፈረንሶችና ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው አምልኮዎች እንዲቋረጡ አሳሰበ። 

ኀብረቱ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) አስመልክቶ አባል ቤተእምነቶች መውሰድ ስለሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃ በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል።

የኀብረቱ ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ እንዳሉት የኀብረቱ ሥራ አመራር ቦርድ በትናንትናው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ አባል ቤተእምነቶች መውሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃ ማሳሰቢያዎችን ሰጥቷል።

በዚህም በመንግስት በኩል ስለበሽታው የተለየ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ ኮንፈረንሶችና ብዙ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው አምልኮዎች ለጊዜው እንዲቋረጡ ሥራ አመራር ቦርዱ ማሰሰቡን ገልጸዋል።

በቤት ውስጥ የሚከናወኑ የጸሎት ስነስርአቶች በተመረጡ ሰፋፊ ቤቶች ውስጥ የሰዎች ርቀት ተጠብቆ ሊከናወኑ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የፀሎት ኀብረትና የመፅሀፍ ቅዱስ ጥናቶች በጥንቃቄና ርቀትን በጠበቀ መልኩ እንዲካሄዱም አስገንዝበዋል።

እድሜያቸው የገፋ አዛውንቶች በመኖሪያ ቤታቸው በግል የሚገለገሉበት ሁኔታ እንዲመቻችና ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ መግለጫዎችን ምዕመናኑ ተግባራዊ እንዲያደርግ ቤተእምነቶች መንገር እንዳለባቸውም ነው ፓስተር ጻዲቁ የገለፁት።

ቤተ እምነቶች በግልም ሆነ በጥቂት ሰዎች ጾምና የጸሎት ሥርአት የሚቀጥሉበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹም አሳስበዋል። 

ሰፋፊ አዳራሽ ያላቸው ቤተእምነቶች የአምልኮ ሥርአታቸውን በጥቂት ሰዎች እንዲያካሂዱ እንዲደረግ ፓስተር ጻዲቁ አሳስበዋል።
"እነዚህ ማሳሰቢያዎች እምነትንና የአምልኮ ስርዓቶችን የሚጋፉ ሳይሆኑ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሚመክሩ በመሆናቸው ተግባራዊ ልናደርጋቸው ይገባልም" ብለዋል።

መፀለይና ምህላ ማድረግ የሚገባ ቢሆንም ጥንቃቄ ማድረግም ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

"የተለዩ የሚመስላቸው ሰዎች እንዳያዘናጉንና በአጉል መንፈሳዊነትና የጥንቃቄ ጉድለት ሰዎችን እንዳይጎዱ መጠንቀቅ ይገባል" ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ባደጉትና በበለፀጉት አገራት ጭምር ፈተና መሆኑን በመረዳት ምዕመኑ ከፀሎት ባሻገር መጠንቀቅ እንዳለበትም ነው ፓስተር ጻዲቁ ያስገነዘቡት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም