የመገናኛ ብዙሃን አባይን በማስተዋወቅ ብዙ አልሰሩም

89

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 ከኢትዮጵያ እንብርት ስለሚፈልቀውና ድንበር አቋራጩ የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያዊያን በማስተዋወቅ በኩል የመገናኛ ብዙሃን ብዙም አለመስራታቸውን አንጋፋው ጋዜጠኛ ፋንታሁን ኃይሌ ተናገረ። 
መነሻውን ከኢትዮጵያ በማድርግ አጠቃላይ 11 አገራትን የሚያካልለው የአባይ ወንዝ ከግብፅ በስተቀር ለሌሎቹ አገሮች እምብዛም ጥቅም ላይ እንዳላዋሉት ይነገራል።

የውሃው መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ደግሞ ከአባይ ወንዝ እስካሁን ተጠቃሚ አይደሉም ተብለው ከሚጠቀሱት አገሮች በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።

ለዚህም ነው "ከዘመናት ዝምታና ውሃው ጅራቱን ይዞ ሲወርድ ከመመልከት ባለፈ" ግድብ በመስራት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የዛሬ ዘጠኝ ዓመት የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታ የጀመረችው።

ሆኖም ይህ የኢትዮጵያ ግድብ መገንባት የአንበሳውን ድርሻ ይዛ በብቸኝነት ሊባል በሚችል መልኩ ውሃውን ለምትጠቀመው ግብፅ እስካሁንም ሊዋጥላት አልቻለም።

የግብፅ ህገ መንግስትም " የናይል ውሃ የግብፅ ብሄራዊ ሃብት ነው፤ የግብፅ መንግስትም የናይል ውሃ ሃብትን የመቆጣጠር፣ የማልማትና ከማንኛውም አሰናካይ ነገሮች የመጠበቅ ግደታ ተጥሎበታል" ሲል ይደነግጋል።

በዚህ ዙሪያ ግብፃዊያን ግንዛቤ እንድኖራቸው የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት አድርገው በመስራት ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ግን በአባይ ወንዝ ላይ አጀንዳ ቀርፀው ለህዝባቸው መረጃ በመስጠት በኩል እምብዛም አልሰሩም ይላል አንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ደራሲ ፋንታሁን ኃይሌ።

ግብጽን የመጎብኘት አጋጣሚ የነበረውና በካበተ የጋዜጠኝነት ልምዱ መፅሃፍ የደረሰው ኢትዮጵያዊዩ ጋዜጠኛ ፋንታሁን "ከግብፆች አንፃር እኛ ብዙም የሰራነው ነገር የለም" ይላል።

የግብፅ መገናኛ ብዙሃን ለህዝባቸው ብሎም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ "ናይል ለግብፅ ፈጣሪ የለገሳት ሃብቷ ነው" በማለት ሲሰብኩ ኖረዋል።

በትምህርት ቤቶችም ግብፃዊያን ከህፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ በካሪኩለም ተቀርፆ እንዲማሩ የሚደረግ መሆኑን ይናገራል።

በኢትዮጵያ በኩል ግን በአባይ ወንዝ ዙሪያ ህፃናት አውቀው እንዲያድጉና አዋቂዎችም ግንዛቤ እንዲኖራቸው ብዙ አልተሰራም ይላል።

ጋዜጠኛ ፋንታሁን እንደሚለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንም ለዜጎችም ሆነ ለሌላው ዓለም የዓባይ መነሻ ኢትዮጵያ መሆኗን እንኳን በቅጡ እያሳወቁ አልመጡም።

በኪነ ጥበብ ዘርፉም አባይ በኢትዮጵያ ብዙ ተሰርቶለታል ለማለት አያስደፍርም ይላል።

ከኢትዮጵያ ሚዲያዎች ጥቂቶቹ በዚህ ዙሪያ ለመስራት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ከግብፆች አንፃር ግን ብዙ መራመድ ይጠበቅባቸዋል ይላል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ይናገራል።

የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለንተናዊ ክንውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ተከታትለው በየጊዜው ለህዝቡ መረጃ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለው ግድብ ህዝቧን ከጨለማ ለማውጣት እንጂ ማንንም ለመጉዳት እንዳልሆነም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስርዳት የሚዲያዎች፣ ፖለቲከኞችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም የሁሉም ዜጎች ሃላፊነት መሆኑን አብራርቷል።

ግድቡን በማስመልከት ለሚደረጉ ድርድሮች የመንግስት ቁርጠኝነትና ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ ወሳኝ መሆኑንም ጋዜጠኛ ፋንታሁን ጠቁሟል።

ግብፅ የተለያዩ የውሃ አማራጮች ያሏት ስለመሆኑና ግድቡም የሚፈጥርባት አሉታዊ ተፅእኖ ባለመኖሩ ለድርድር መቅረብ እንዳልነበረባትም ያምናል።

ኢትዮጵያ ከራሷ በተጨማሪ ለአካባቢው አገራት የሃይል አማራጭ ለመፍጠርና የመሰረተ ልማት ትስስር እውን ለማድረግ ጥረት በማድርግ ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም