የአንበጣ መራቢያን ለመከላከል የአሰሳና ቅኝት ስራ እየተሰራ ነው

46

ባሕርዳር መጋቢት 15/2012 በአማራ ክልል የአንበጣ መንጋ ተፈልፍሎ መልሶ ሥጋት እንዳይፈጥር የመራቢያ ቦታዎችን በመለየት የቅኝትና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ባለፈው ጥር ወር ወደ ክልሉ የገባው የአንበጣ መንጋ 134 ሺህ ሄክታር በሰብል የለማ መሬት መውረሩን የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ ለኢዜአ አስታውሰዋል።

የአንበጣ መንጋውን አርሶ አደሩ የተለያዩ ባህላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መከላከል እንደተቻለ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የአንበጣ መንጋ አለመኖሩን ጠቅሰው በቀጣይም መልሶ እንዳይከሰትና በበልግና በመስኖ የሰብል ልማት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም ለአንበጣው መራቢያ አመቺ የሆኑ ሸለቋማ፣ ጎርጆችና አሸዋማ ቦታዎች በመለየት በባለሙያዎችና በአርሶ አደሩ የተጠናከረ የአሰሳና ቅኝት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከመስኖና በልግ ሰብል በተጨማሪ በቀጣዩ የመኽር ወቅት የአንበጣው መንጋ ጉዳት እንዳያደርስ ከ25 ሺህ ሊትር በላይ ኬሚካልና ተያያዥ ግብአቶችን ከወዲሁ የማቅረብ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ በበኩላቸው በአፋር ክልልና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ ቦታዎች መንጋው ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን ገልጸዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ዝናብ እየጣለ በመሆኑ መንጋው ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት በማሳደሩ የሚደረገው የአሰሳና ቅኝት ሥራው ተጠናክሯል።

ለዚህም ከአዋሳኝ ቦታዎች በተጨማሪ በወረባቦ ጫሊ፣ በቃሉ ዜሮ 19 እና በአምባሰል ጨፌ ቀበሌዎች ለመንጋው መራቢያ አመቺ ናቸው የተባሉ ጎርጆችና አሸዋማ ቦታዎች ዕለት ከዕለት በግብርና ባለሙያዎችና በአርሶ አደሮች ክትትል እየተደረገ ይገኛል።

በአካባቢው ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ጭንቀት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር ያወሱት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የዜሮ 15 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኡስማን ጀማል ናቸው።

መንግሥት ኅብረተሰቡን አስተባብሮ ባደረገው የተጠናከረ የመከላከል ሥራ ሰብላቸውን በከፊል ከውድመት እንደታደገላቸው ገልጸዋል፡፡

አሁንም በመስኖ እያለሙት ያለው አትክልትና ፍራፍሬ የአንበጣ መንጋ ተከስቶ እንዳያወድምባቸው ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመሆን ማሳቸውንና አሸዋማ ቦታዎችን ዘወትር እያሰሱ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የሰብ ሸንጎ ቀበሌ አርሶ አደር ውዱ ቀረብህ በበኩላቸው በቅርቡ በአካባቢያቸው የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በባሕላዊ መንገድ ድምፅ በማሰማትና ጅራፍ በማጮህ እንዳባረሩት ገልጸዋል።

አሁን አካባቢው ከአንበጣ ነፃ ቢሆንም አርፎባቸው በነበሩ የአባይ ሸለቋማ ቦታዎች እንዳይፈለፈል አርሶ አደሩ በአደረጃጀት ጠዋትና ማታ አሰሳ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

በክልሉ ከመስከረም መጨረሻ እስከ ታኅሣሥ ወር 2012 ዓ.ም ድረስ በመጀመሪያው ዙር ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ከአራት ሺህ ሄክታር በላይ የደረሰ ሰብል ሙሉ በሙሉ ማውደሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም