በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ የነበረው ታላቁ ሩጫ ለሌላ ጊዜ ተላለፈ

100

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኢዜአ) በአሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ በየዓመቱ ይካሄድ የነበረው ታላቅ ሩጫ ውድድር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጥቅምት ተላለፈ።

በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ በሦስት ከተሞች ተገኝተው፣ ከተፈጠረው ለውጥ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያውያን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በዋሽንግተን በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢትዮጵያውያን ፕሮግራም  የከተማዋ ከንቲባ መሪያል ባውሰር ቀኑን ‹‹የኢትዮጵያውያን ቀን በዲሲ›› ተብሎ እንዲከበር መወሰናቸውም አይዘነጋም።

የመጀመሪያው ዝግጅትም ባለፈው ሃምሌ 2011 ዓ.ም  ከ20 የሚበልጡ ኢትዮጵያን ወክለው በኦሎምፒክና ዓለም ሻምፒዮና ላይ የተሳተፉ ታዋቂ አትሌቶች፣ አርቲስቶች፣ አምባሳደሮች በተገኙበት መካሄዱ ይታወቃል።

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አና አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ መሸለማቸውም እንዲሁ የሚታወስ ነው።

በዚህ ዓመትም፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ አትሌቶችና  በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ አትዮጵያዊያን ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በሃምሌ ወር ሊደረግ የታሰበ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረሽኝ ምክንያት ወደ ጥቅምት ተራዝሟል።

የዝግጅት ክፍሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት አለም ባጋጠማት የኮቪድ19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን አስታውቋል።

በወረርሽኙ ምክንያት ዝግጅቱን ማካሄድ አስቸጋሪ ወይም የማይቻልበት ሁኔታ ከተፈጠረም ለተጨማሪ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል አዘጋጆቹ ገልጸዋል። 

በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንዳሉት፤ እያንዳንዱ ሰው የሚወስዳው ጥንቃቄ እና እርምጃ የቫይረሱን የመሰራጨት መጠን በስፋት እንደሚቀንስው ተናግረዋል።

በተለይ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የኮቪድ 19ን ሥርጭት ለመግታት የሚያግዝ አንዱና ዋነኛው መንገድ መሆኑን ተናግረው ሁሉም ራሱንና ቤተሰቡን ከቫይረሱ በመጠበቅ ስርጭቱን ለማቆም እንዲረባረብ ጠይቀዋል።

ውድድሩ የተራዘመው በዲሲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በፍጥነት ተገትቶ ውድድሩ በተባለበት ጊዜ ከተካሄደ "ይህንን ፈታኝ ጊዜ በጋራ መወጣታችንን ተሰባስበን የምናከብርበት ኣጋጣሚ አንደሚሆን አምናለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በበኩሏ  የውድድር ጊዜው መተላለፉን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየት "ቅድሚያ ለጤና" በመሆኑ  አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና እጅ በመታጠብ የራስን ብሎም የሌሎችን ህይወት ከወረሽኙ መጠበቅ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፋለች። 

በሚቀጥለው ዝግጅት ላይ ተገኝታ ከኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር  መልካም ጊዜ እንደምታሳልፍ ገልፃለች።

የውድድሩ አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ በበኩላቸው ማህበረሰቡ ይህንን ፈታኝ ጊዜ የጤና ባለሞያዎችን ምክር በመከተል እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል።

በውድድሩ ላይ በሁሉም ዘርፍ በተሻለ እና በተደራጀ መልኩ ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንደሚሳተፉበት ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም