በኢትዮጵያ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋ ስጋት ሆኗል

59

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14/2012 (ኢዜአ) ከኬንያና ከሶማሌ ላንድ የሚገባው የአንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ተከስቶ የመከላከል ስራ እየተሰራ ቢሆንም በበልግ አብቃይ አካባቢዎችም ከፍተኛ ስጋት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት በበኩሉ በምስራቅ አፍሪካ የአንበጣ መንጋ ጉዳት እያደረሰባቸው ካሉ አገራት ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን ገልጿል።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት ከአጎራባች አጋራት የሚመጣውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።

ሆኖም በልግ አብቃይ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የአንበጣ መንጋው ስጋት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

በተለይ ከኬንያ የሚገባው የአንበጣ መንጋ በቦረና እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች በሰብልና በእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ችግሩን ለመከላከል ሰባት አውሮፕላኖችን 34 የመድሃኒት ማመላለሻ መኪኖችንና ባለሙያዎችን በማሰማራት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የመከላከሉን ስራው ከባለሙያዎች ባለፈ ህብረተሰቡ በንቃት በመከታታል መረጃዎችን የማቀበልና በጋራ የመከላከል ስራ ይጠይቃል ብለዋል።

ወቅቱ ለአንበጣ መንጋው መስፍፋትና መፈልፈል ጥሩ አጋጣሚ ስለሚፈጥርና አንበጣው የሚገባው በብዛት ሰው በማይኖርባቸው ድንበር አካባቢ በመሆኑ የመከላከል ስራውን ፈታኝ ያደርገዋል ነው ያሉት።

በተለይ በአገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ክልሎች በየአካባቢያቸው ግብረ ሃይል በማቋቋም የችግሩን ስፋት መቀነስ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ችግሩን መድሃኒት በመርጨት ብቻ መከላከል ስለማይቻል በአካባቢው የሚገኙ አርብቶ አደሮችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።


ከኬንያ የሚገባው የአንበጣ መንጋ በቦረና እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች በሰብልና በእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

በተመሳሳይ በሶማሌ ላንድ የገባው የአንበጣ ኩብኩባ ደግሞ በደቡብ ኦሞ ዞን፣  ሐመር፣  ዳሰነች፣ ጸመይ ወረዳና በኮንሶ ዞን ተከስቷል።

አብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ በልግ አብቃይ በመሆኑና እስከ ሰኔ መጨረሻ ሰብል በማሳ ላይ ስለሚቆይ መንጋው በአግባብ ካልተከለከሉ ጉዳቱ የከፋ እነደሚሆንም ተመልክቷል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የአሰሳ ጥናት ማካሄድ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ፋጡማ ሰኢድ የአንበጣ መንጋው በምስራቅ አፍሪካ  ዘጠኝ አገራት መከሰቱን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የአካባቢው አገራት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ድጋፋቸውን አጠናክረው በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

አገራቱን በምግብ እህል እራሷን ለመቻል የሚተታደርገውን ጥረት እንዳይጎዳ የአገራት ድጋፍ ወሳኝ ነውም ብለዋል።

ድርጅቱ መንጋው በአገራቱ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን በቅርቡ ለመድሃኒት መርጫ የሚሆን ሁለት አውሮፕላኖችን ሰጥቷል።

በቀጣይም ሶስት ተጨማሪ አውሮፕላኖችን እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም