የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ጃክ ማ የአፍሪካ አገሮችን ለመደገፍ ቃል የገቡት ቁሳቁሶች አዲስ አበባ ደረሰ

48

አዲስ አበባ፤መጋቢት 13/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ የአሊባባ መስራች ጃክ ማ የአፍሪካ ለመደገፍ ቃል የገቡት ቁሳቁሶች ዛሬ አዲስ አበባ ደርሷል። 

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታትና የአፍሪካ አገሮች በበሽታው ቅድመ መከላከል ላይ እንዲበረቱ የአሊባባ  መስራቹ  ጃክ ማ ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ያደረጉት ድጋፍ ዛሬ አዲስ አበባ ደርሷል።

ካደረጉት ድጋፍ መካከል 100 ሺህ የፊት መሸፈኛ ጭንብል፣ 20 ሺህ የሙቀት መለኪያ መሳሪያና ከ1 ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎች ሙሉ አልባሳት ይገኝበታል።

በኢትዮጵያ የድጋፉ አስተባባሪ ዶክተር ሹመቴ ግዛው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ድጋፉ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ ችሏል።

አዲስ አበባ የደረሰው ቁሳቁስ ለ54ቱም የአፍሪካ አገሮች ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮ እንደሚሰራጭ ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ሹመቴ ገጻ፤ 90 በመቶ የሚሆኑት ቁሳቁሶች የገቡ ሲሆን ስርጭቱም የሚደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የስርጭቱን ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት ገለጻ፣ ድጋፉ ወደ አገሮቹ በመደበኛ የመንገደኞች መጓጓዣና በጭነት አውሮፕላኖች ይደርሳል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ድጋፉ በአፍሪካ አገሮች የሚደረገውን የቅድመ መከላከል ስራ የሚያግዝና የስርጭቱን መጠን ለመቀነስ ሚናው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም