የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችን አጠናክረን እንቀጥላለን - የዲላ ከተማ ነዋሪዎች

62

ዲላ፣ መጋቢት 12/ 2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ድጋፋቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበት አማራጭ እንዲፈጠርላቸው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ ።

ኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡት የዲላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የመንግስት ሰራተኛው አቶ አብዱልካፍ ሁሴን እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ለሶስት ጊዜያት ያህል ከደመወዛቸው በመቁረጥ የህዳሴ ግድብ ቦንድ ገዝተዋል።

በግንባታው ሂደት የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት እንደሚያወግዙ የገለፁት አቶ አብዱልካፍ በ8100 ኤ ብቻ የሚደረገው የገቢ ማሰባሰብ ስራ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች አማራጮች እንዲታከሉበት ጠይቀዋል ። 

በንግድ ሰራ የተሰማሩት ወይዘሮ ሳራ ወጋየሁ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላ ህዝቡ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ዶክተር መላኩ ጌታሁን በበኩላቸው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚደረግ የገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለግንባታው መጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ሎተሪ ፣ የቦንድ ግዥና ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ መድረኮችን በማዘጋጀት በህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን መነቃቃት ማጠናከር እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም