ፋኦ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የአንበጣ መከላከያ አውሮፕላን ድጋፍ አደረገ

66

መጋቢት 12/2012 ኢዜአ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ለአንበጣ መከላከያ የሚያገዝ ተጨማሪ የመድሃኒት መርጫ አውሮፕላን ድጋፍ አደረገ።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ፋጡማ ሰኢድ በአገሪቷ የበረሃ አንበጣ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ባለፈው ወር ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ "ዛሬ አንድ አውሮፕላን አስረክበናል" ብለዋል።

ተጨማሪ ሶስት የመድሃኒት መርጫና መረጃ ማሳባሰቢያ አውሮፕላኖች በቅርቡ እንደሚያስረክቡም ተናግረዋል።

ድርጅቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል አገራቱ እያደረጉት ያለውን ጥረት በገንዘብና በቁሳቁስ ሲያግዝ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋውን መከላከያ መድሃኒት ጨምሮ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎችና ሌሎች ድጋፎችን በቀጣይም እንደሚደርግ አስታውቀዋል።

ድርጅቱ የበረሃ አንበጣው በቁጥጥር ስር እስከሚውል ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ወይዘሮ ፋጡማ የተናገሩት።

አውሮፕላኑን የተረከቡት የግብርና ሚኒስትር ኡመር ሁሴን እንዳሉት የበረሃ አንበጣ ከሌሎች አገራት በመግባት በሰብል፣ በእንስሳት መኖ እና በእጽዋት ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል።

መንጋውን ለመከላከል የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል።

መንግስት በኪራይ ባሰማራቸው አራት አውሮፕላኖች ላይ ከፋኦ በድጋፍ የተገኙ ሁለት አውሮፕላኖችን በማከል የመከላከል ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

የተደረገውን ድጋፍ በአግባቡ በማስተዳደርና በመጠቀም የበረሃ አንበጣ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በቅንጅት እንደሚሰራም አክለዋል።

አውሮፕላኖቹ የአንበጣው መንጋውም መቆጣጠር እስከሚቻል ድረስ በኢትዮጵያ ይቆያሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም