የግድቦችን የአገልግሎት ዘመን ለማራዘም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

114

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 12/2012 ( ኢዜአ) ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ የሌሎች ግድቦችን የአገልግሎት ዘመን ለማርዘም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራን ማጠናከር እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ሥራዎች አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠሉ ግድቦች በደለል የመሞላት ዕድላቸው ሰፊ እንደሚሆንም ተገልጿል።

የተፋሰስ ልማት ሥራ የተራቆተ መሬት እንዲያገግም ከማድረግ ባለፈ ያልተራቆተ መሬት በአግባቡ እንዲያዝና ስነ-ምህዳሩ ተፈጥሯዊ ጥቅም እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው።

በኢትዮጵያ ዓባይን ጨምሮ የተለያዩ ወንዞች በደን ጭፍጨፋ ምክንያት በሚከሰት የስነ-ምህዳር መዛባት የውሃ መጠናቸው እየቀነሰ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህም በተለይ ወንዞቹን ተከትለው የሚገነቡ የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በተያዘላቸው ጊዜ ሥራ እንዳይጀምሩና ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዳይሰጡ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።


የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት እንዲቆራረጥና ግድቦች በደለል እንዲሞሉ በማድረግ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ መሆኑንም ነው የገለጹት።


በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ተቋም መምህርና የውሃና መሬት ሃብት ልማት ማዕከል ተመራማሪ ዶክተር አማረ ባንቲደር በአሁኑ ወቅት  ያለው የአፈር መሸርሸር የሚቀጥል ከሆነ የሕዳሴ ግድቡን ዕድሜ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳዋል ብለዋል። 


"እንደ ጥናታችን ውጤት ከሆነ አሁን የሚሄደው ደለል የሚገባ ከሆነ የሕዳሴ ግድቡ ምርት ማምረት ከጀመረ ከ20ኛው ዓመት ጀምሮ የምርት ማሽቆልቆል ዕጣ ይደርሰዋል" ብለዋል። 

ሆኖም ተፋሰሶች በአግባቡ ከለሙና  አሁን ያለው የአፈር መሸርሸር በ70 በመቶ ከተቀነሰ  የሕዳሴ ግድቡ ዕድሜ ከ374 ዓመት በላይ ሊሆን ይችላል ሲሉም ተናግረዋል።

በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን የሬድ ፕላስ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስም ይህንኑ ነው የሚያረጋግጡት።

በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ግድቦችና ለመስኖ የሚሆኑ ወንዞች ተፋሰስ  አካባቢዎች ልቅ ግጦሽ መኖሩንና ደኖች እየለሙ አለመሆኑንም ተናግረዋል።  

ይህም አካባቢዎቹ በደለል እንዲሞሉ የሚያደርግ መሆኑንና  የህዳሴው  ግድብን  ጨምሮ  የሌሎች ግድቦችን የአገልግሎት ዘመን ዕድሜ ሊያሳጥር  እንደሚችል  ነው ያብራሩት። 

የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ የኅብረተሰብ ብልጽግና መሰረት መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎቹ ፤በተለይ ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ዘላቂና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲሰጡ የአካባቢውን ስነ-ምህዳር መጠበቅ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተለይ የዓባይ ወንዝ የውሃ መነሻዎች ላይ አደጋ እንዳይጋረጥ አካባቢዎቹን በደን ማልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ መስራት ወሳኝ መሆኑን ነው ያነሱት።

ዶክተር ይተብቱ ሞገስ የዓባይ ወንዝ የውሃ መነሻው በዋናነት የኮንጎ ደን በሚለቀው ትነት መሆኑን ገልጸው ፤ ምዕራብ አፍሪካ ላይ ያለው ደን ከጠፋ የዓባይ ውሃም ይጠፋል ብለዋል። 

ይህ ጉዳይ አጀንዳ ተደርጎ በአፍሪካ ኅብረት ደረጃ የተፋሰሱ አገራት ያለውን ውሃ  በደንብ መያዝ የሚችሉባቸው  መንገዶችና  የደን  ልማት ላይ በጋራ  መስራት  ይኖርባቸዋል ብለዋል።  

በኢትዮጵያ በቂ የደን ልማት ባለመኖሩ በበጋ የውሃ እጥረት፤ በክረምት ደግሞ የጎርፍ አደጋ ማጋጠሙ የተለመደ ሆኗል።

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ በመንግስትና በኀብረተሰቡ ተሳትፎ በየዓመቱ በበጎ ፍቃድ የሚደረገው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ከተፋሰስ ልማቱ የሚመነጨው ሃብትም የተፋሰስ ስራውን በዘላቂነት ማገዝ እንዳለበት ነው ያስረዱት።

የግብርና ሚኒስቴር፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የደን አካባቢና አየር ንብረት ኮሚሽን ሥራዎችን በጋራ ማካሄድ እንደሚገባቸውም አንስተዋል። 

በክልሎችም በተለይም በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ የአማራ ክልል፣ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል በጋራ ተናበው መስራት ይኖርባቸዋል በማለት ሌሎችም ሲቪክ ማኅበረሰቡና ኅብረተሰቡም ተቀናጅተው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ የመሬትና የእርሻ አያያዝ ላይ፣ የደን ልማትና  ሌሎች  ልማቶች  ላይ የህብረተሰብ ንቅናቄ መፍጠርና ባለሙያ በመመደብ  መስራት  እንደሚያስፍልግም ገልጸዋል። 

ይህም አፈር እንዳይሸረሸርና ደለል እንዳይኖር በማድረግ ግድቦች ንጹህ ውሃ እየተቀበሉ ዕድሜያቸው ረጅም ሆኖ የኃይል ምንጭ እንዲሰጡ ያስችላል ነው ያሉት።  

በተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የወንዝ አመራር ዳይሬክተር አቶ ደጀኔ ለገሰ ባለስልጣኑ በዓባይ ተፋሰስ ዙሪያ አራት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በስምንት ሺህ ሄክታር መሬት 40 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከልም
መታቀዱን ገልጸው፤ እስካሁንም 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞች መፍላታቸውን ገልጸው፤ በቀሪው ጊዜም ዕቅዱን በማሟላት ችግኞችን በማፍላት ተከላ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።


"በተያዘው ዓመት የክረምት ወራት በመላ አገሪቷ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዷል" ብለዋል።

ባለፈው ክረምት በመላ አገሪቷ 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ፤ በአንድ ቀን ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው የዓለም መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ማለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም