የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ባህላዊ የግጭት አፈታትን በማዳበር ለሰላም መጠናከር ሊሰሩ ይገባል

113
ሐረር ሰኔ 23/2010 " የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ባህላዊ የግጭት አፈታትን በማዳበር  ለሰላምና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መጠናከር ሊሰሩ ይገባል" ሲሉ የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገለጹ። የአምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የባህላዊ ግጭት አፈታት ስርዓት የጋራ የውይይት መድረክ ዛሬ በሐረር ከተማ ተጀምሯል። አፈ ጉባኤዋ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ብዝሃነት ሳይሸራረፍ አንድነትን ለማጠናከር የሚቻለው ሁሉም አካላት ለሰላም  ሲንቀሳቀሱ ነው። በሀገሪቱ የሚከሰትን የጸጥታ ችግር ለመፍተት  የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል። " ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን በማዳበር  ለሰላምና ዴሞክራሲያዊ አንድነት መጠናከር ሚናቸውን መወጣት አለባቸው " ብለዋል። የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አብዱል ማሊክ በከር በበኩላቸው አምስቱ አጎራባች ክልሎች የየራሳቸው የግጭት አፈታት ዘዴ ያላቸው በመሆኑ ይህን በተገቢው መንገድ ተጠቅመው ሰላምን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። የውይይት መድረኩ ለሁለት ቀን የሚቆይ ሲሆን የአምስቱ  አጎራባች ክልሎች የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፣አፈ ጉባኤዎች እንዲሁም የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ በቆይታቸውም ባህላዊ የግጭት አፈታት ላይ ያተኮረ ጽሁፍ በባለሙያ  ቀርቦ ውይይት ይካሄዳል፤ በዚህ ላይ የተሰሩ መልካም ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም