የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ቀናት ሽግሽግ አደረገ

72

ሐረር፣ መጋቢት 11/2012 ( ኢዜአ) የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ስራ ቀናት ሽግሽግ ማድረጉን አስታወቀ።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ  ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። 

ቫይረሱ  የሚተላለፈው በሰዎች መካከል ንክኪና በተጠጋጋ ግንኙነት በመሆኑ ከፍርድ ቤት ዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ የስራ ባህሪ አንጻር ለመከላከል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች የስራ ቀናት ሽግሽግ እንዲደረግ ውሳኔ ማሳለፋቸውን መግለጫው አትቷል።

በዚህም ፍርድ ቤቶቹ  ከመጋቢት 14 እስከ መጋቢት 25/ 2012 ዓ.ም. ድረስ ተቀጥረው የነበሩ መዛግብት ከመጋቢት 25/2012 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ቀናቶች እንደ የጉዳያቸው እየታየ በቀጠሮ እንደሚሸጋሸጉ ተገልጿል።

ዳኞች የሚሰጧቸውን ተለዋጭ ቀጠሮዎች ተከራካሪ ወገኖች እንዲያውቁት ለማድረግ በፍርድ ቤት ግቢዎች የመዝገቦች ዝርዝርና የቀጠሮ ቀኖች እንዲለጠፉ ይደረጋል።

በአጋጠመው አስገዳጅ ሁኔታ ቀጠሮ በመተላለፉ ምክንያት ወደ ፊት ሊያጋጥም የሚችለውን ክምችት ለመቀነስ ዳኞች በስራ ገበታቸው ላይ ትኩረት አድርገው በሙሉ አቅማቸው ለውሳኔ የደረሱ መዝገቦች ላይ እልባት እንደሚሰጡ ተገልጿል።

ፍርድ ቤቶች አዲስ መዝገቦች ፣ የጊዜ ቀጠሮ ፣ የዋስትና ፣ቀለብና ሌሎች መሰል አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን  ያስተናግዳሉ።

የክልሉ ፍርድ ቤት የችሎት ስራዎች እንዲሸጋሸጉ የተወሰነው ወደ ፍርድ ቤቱ የሚመጡ ተገልጋዮች ፍሰት ለመግታት መሆኑን  በመግለጫው ተመላክቷል።

የፍርድ ቤቱ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች በተመለከተም አካል ጉዳተኞች ፣ ነፍሰ ጡሮች ፣ የስኳር ህሙማንና  ሌሎች የታወቀ ህመም ያለባቸው  እረፍት እንዲሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።

ማንኛውም ባለ ጉዳይ ተጨማሪ ማብራርያ ካስፈለገው ወደ ፍርድ ቤቱ መምጣት ሳያስፈልገው በ0256660300 ፣ 0915757242 እና 0975365438 ሞባይል የስልክ ቁጥሮች መረጃ ማግኘት እንደሚችል ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም