የአርሲ ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ ግንባታዎችና የማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ ነው

483

አዳማ  መጋቢት 11/2012  (ኢዜአ) የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ብር በሆነ በጀት አዳዲስ ግንባታዎችና የማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ። 

ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱ በጥናትና ምርምር የተደገፈ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑም ተመልክቷል።

በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት  ዳይሬክተር ዶክተር ገመዳ ሁንዴ ለኢዜአ እንዳሉት አዳዲስ ግንባታዎቹ የሚናወኑት  ዲንሾ የኢንጅነሪንግና ተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም ቦቆጅ የሶሻል ሳይንስና ሂውማኒት ካምፓሶች ውስጥ ነው።

ማስፋፊያው ደግሞ በጤና ሳይንስና ግብርና ኮሌጅ ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰው አዳዲስ ግንባታዎችን ጨምሮ   ሥራዎቹ 95 በመቶ መጠናቀቃቸውን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱ በጥናትና ምርምር የተደገፈ እንዲሆን እየተሰራን መሆኑን ጠቁመው “የአርሲ ዞን በሰብል ልማት ግንባር ቀደም በመሆኑ የምርምር ሥራችን በዚህው ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል።

ከምርምር ስራዎቹም  ስንዴ፣ገብስ፣ ጥራጥሬና ቅመማ ቅም ሰብሎች ላይ ይገኙበታል።

በዩኒቨርስቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ መርጋ ባዩ በበኩላቸው ተቋሙ  በጤና ዘርፍ በተለይ በቆላ በሽታና በመድሀኒት ቅመማ ላይ እስከ አሁን ከ60 በላይ የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በምርምር የተገኙ ውጤቶች በዩኒቨርሲቲው የጤና ዘርፍ ትምህርት ጥራት ለማስጠበቅና ተግባር ተኮር የሆነ ትምህርትና ስልጠና ተማሪዎቹ እንዲያገኙ እያገዙን ነው ብለዋል።

በተለይ በአሰላ ሪፌራል ሆስፒታልና በዞኑ የሚገኙ የጤና ተቋማት የአግልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል ለማድረግ የምርምር ውጤቶቹ አግዘዋል።

“በዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተካሄዱት የጥናትና ምርምር ሥራዎች በዘርፉ ከተሰማሩ የውጭ ሀገር ድርጅቶችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንዲንሰራ አስችሎናል “ብለዋል።

በዚህም ከውጭ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውን የተለያዩ የህክምን መርጃ መሳሪያዎች፣ ድጋፍ ማግኘታቸውን ያመለከቱት አቶ መርጋ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሰረታዊ ለውጥ እየመጣ መሆኑን  ተናግረዋል።

ለአሰላ ሆስፒታል፣ በአርሲ ዞን ሥር ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና አራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የህክምና መርጃ መሳሪያ በ200 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲሟሉ ተደርጓል ብለዋል።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ  ከ13ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመቀበል በመማር ማስተማር ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።