በውጭ ሀገራት የሚሠሩ አፍሪካውያን ለአህጉሪቷ እድገት እምቅ አቅም አላቸው…ጥናት

179

መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) በውጭ ሀገራት የሚኖሩ አፍሪካውያን ለአህጉራቸው ሁለንተናዊ እድገት ያልተነካ እምቅ አቅም እንዳላቸው ሱድዊንድ የተሰኘ ድረገጽ ዓለም አቀፍ የጥናት ተቋምን ጠቅሶ ዘገቧል፡፡

በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ ለትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የሚኖራቸው አስተዋጾ ከፍተኛ ቢሆንም አፍሪካዊያን በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ በቦንድና በመሳሰሉት የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ላይ በማሳተፍ ረገድ ውስንነቶች እንዳለባቸው ጥናቱ ጠቁሟል።

ኢትዮጵያ ዲያስፖራውን በማሳተፍ ረገድ ውጤቱ የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም እንደተሳካላት ጥናቱ አመልክቷል።

አፍሪካዊያን ዜጎች በሀገራቸው በቂ የሥራ እድል ባለማግኘታቸው ምክንያት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ስደትን አማራጭ አድርገው ባገኙት የሥራ እድል ያገኙትን ገንዘብ ወደ ሀገራቸው በመላክ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚደጉሙ ያስታወሰው ጥናቱ፤ በዚህም ከ8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች እንደሚተዳደሩ አመልክቷል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ወደ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገሮች እንደተላከ የሚያመለክተው ጥናቱ፤ ገንዘቡን የተጠቀሙት የተላከላቸው ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ጭምር እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል።

እነዚህ ሀገራት ለልማት ፕሮጀክቶቻቸው የዲያስፖራ ቦንድ ሽያጭን አይነተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አካል ሊሆን እንደሚችል አጥኝዎቹ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ህንድ፣ ባንግላዲሽ፣ ሊባኖስ፣ ሲሪላንካና ፊሊፒንስ የመንግሥታቸውን የልማት ፕሮጀክቶች በመደገፍና መንግሥታቸውም የተላኩትን ገንዘቦች በውጤታማነት በማስተዳደር ምርጥ ተሞክሮ እንዳላቸው ጥናቱ አመልክቷል።

በአፍሪካም ይሄ ተሞክሮ እንዲሠራ በውጭ የሚኖረው አፍሪካዊ ዲያስፖራ በሀገሩ መንግሥት ላይ እምነት እንዲኖረውና በልማቱ ሥራ ላይ እንዲሳተፍና ሀገራዊ ፍቅር እንዲኖረው መሥራት እንደሚገባም ተመልክቷል።

በተቃራኒው በአፍሪካ ይሄ አይነቱ ተሞክሮ ያላቸው ሀገራት ጥቂት እንደሆኑ የሚናገረው ጥናቱ፤ ጥቂት ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷናት ብሏል።

የዶ/ር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ኢትዮጵያ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቿ ገንዘብ የማሰባሰብ ጥሩ የሚባል ውጤት እንዳገኘች ያነሳው ጥናቱ፤ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በቀን አንድ ዶላር በመለገስ በቤት ውስጥ የጤና እንክብካቤ እና የውሃ አቅርቦትን ለማስፋፋት እንዲሁም ለአነስተኛ ስራዎች ፈጠራ እንዲረዳ ታስቦ በተዘጋጀው መርሃ ግብር እኤአ እስከ ግንቦት 2019 ድረስ 4 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሷል ፡፡

ኬኒያና ናይጄሪያን ለማነጻጸሪያነት ያቀረበው ጥናቱ፤ ኬኒያ እኤአ በ2009 ለገበያ ካቀረበችው የቦንድ ሽያጭ 164 ሚሊዮን ዩሮ በማግኘት ለትራንስፖርት፣ለነዳጅ፣ እና ውሃ ፕሮጀክቶች ያዋለች ቢሆንም፤ ከዚያ በኋላ በተከታታ ለዲያስፖራው ያቀረበቻቸው ቦንዶች የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጡ አስረድቷል።

በአንጻሩ ናጄራዊያን ዳያስፖራዎች በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2018 ከ25 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወደ ሀገራቸው በመላክ የመንግሥታቸውን የመሠረተ ልማት አውታሮች መደገፋቸውን ጥናቱ አመልክቷል።