በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 62 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተዘጋጁ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 62 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተዘጋጁ

ባህርዳር( ኢዜአ) መጋቢት 10/2012 በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዙ 62 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የክልሉ የኮሮና ቫይረስ ተከላካይ ግብረ ኃይል አስታወቀ።
የግብረ ኃይሉ ፀሐፊና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት በሽታውን ለመከላከል በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ ነው።
እስካሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች 62 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች ተዘጋጅተው በግብአት እንዲሟሉ መደረጉን ገልጸዋል።
ወደ ክልሉ የሚገቡ ሰዎች ከበሽታው ነፃ መሆን አለመሆናቸውን ለመለየትም በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላና ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያዎች የልየታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በየብስ ደግሞ ደጀን፣ ደብረብርሃንና ባቲ አከባቢዎች ተጨማሪ የልየታ ቦታዎችን በመክፈት ስራ ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል።
እስካሁንም በአውሮፕላን ማረፊያና በየብስ አከባቢዎች አንድ ሺህ 908 የሃገር ውስጥና የውጭ ተጓዦችን በመሳሪያ የመለየት ስራ መከናወኑን ዶክተር መልካሙ አስታውቀዋል።
ከነዚህም በበሽታው ተጠርጥረው በመቆያ ከነበሩ ስድስት ሰዎች መካከል አራቱ በተደረገላቸው ምርመራ ከበሽታው ነፃና ቀሪዎቹ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢና በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው ሶስት አብይና አምስት ቴክኒካል ኮሚቴዎች እስከ ወረዳ ድረስ ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ሃብት የማፈላለግና ህብረተሰቡን በግንዛቤ ፈጠራ ተደራሽ የማድረግ አብይ ግብረ ኃይሎች መቋቋማቸውንም አመልክተዋል።
በሽታውን ለመከላከል የሚያግዝ ለመነሻ የሚሆን በጀትም የክልሉ ካቢኔ 150 ሚሊዮን ብር መድቦ ትናንት ይፋ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በሽታውን ለመከላከል መንግስት ብቻውን የማይወጣው በመሆኑም አጋር ድርጅቶችና ባለሃብቱ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
"ሁሉም ህብረተሰብ በሽታውን በመከላከል በኃላፊነት ሊንቀሳቀስ ይገባል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማህተመ ኃይሌ ናቸው።
ህብረተሰቡ ሳይረበሽና ሳይዘናጋም ተገቢ ከሆኑ ምንጮች ትክክለኛ መረጃ ወስዶ በቂ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።