የዲላ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ የትምህርት ጥራት ችግር ለማቃለል እየሰራ ነው

192

ዲላ (ኢዜአ) መጋቢት 10/2012 በደቡብ ክልል በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለማቃለል የመምህራንን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የዲላ መምህራን ማሰልጠኛ ኮለጅ ገለጸ።
አንደኛ  ዙር ክልል አቀፍ የትምህርት ጥራት የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

የኮሌጁ ዲን ተወካይ አቶ ደሳለኝ ወቴ በሲምፖዚየሙ ላይ እንደገለጹት በክልሉ በ1ኛ ደረጃና በቅድመ መደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ላይ የጥራት ችግር እንዳለ ኮሌጁ ባካሄደው ጥናት አረጋግጧል።

ተከታታይነት ያለው የመምህራን አቅም ግንባታ አለመኖርናና የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ለትምህርት ጥራት መጓደል ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል ብለዋል።

በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ለችግሩ መፍትሄ በሚሰጥ መልኩ እጩ መምህራንን ለማፍራት ኮሌጁ በዚህ ዓመት ጥረት መጀመሩን ገልጸዋል።

የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየሙ መካሄድ በዘርፉ ያሉትን የጥራት ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለማመላከት አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

ጥናትና ምርምሮች ከሸልፍ ወጥተው በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በጎ ተጽእኖ እንዲፈጥሩና ትምህርት ቤቶች ጋር እንዲደርሱ መሰል መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል ።

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክልሉ በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከስርዓተ ትምህርት አንስቶ እሰከ አደረጃጀት ድረስ ያሉት ችግሮች ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ችግሮቹን በጥናትና ምርምር በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ ከማምጣት ባለፈ ለተግባራዊነቱ የትምህርት አመራሩ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

ከተሳታፊዎቹ መካከል መምህር አስታረቀኝ ተስፋዬ እንደሚሉት በ1ኛ ደረጃ በተለይም በቅድመ መደበኛ ትምህርት የህጻናቱን የመረዳት ደረጃ ያላገናዘበ ትምህርት ሲሰጥ በስፋት ይስተዋላል።

ይህም በህጻናቱ የመማር ፍላጎት ላይ አሉታዊ ተጽኖ ከማሳደሩም ባለፈ የሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ ላይ ጥሰት መፈጸሙን ይናገራሉ።

ችግሩን በጥናትና ምርምር በመለየት ለችግሩ ምላሽ በሚሰጥ መልኩ እጩ መምህራንን ከማፍራት ጎን ለጎን በግብዓትና በአደረጃጀት ረገድ ያሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ መፍታት ይገባል ብለዋል።

በዲላ መምህራን ኮሌጅ የጥናትና ምርምር ማዕከል አስተባባሪ መምህር በፍቃዱ ለገሰ በበኩላቸው በ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመምህራንና የተማሪዎች የግንዛቤ ችግር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ አጋዥ የሆነው ተከታተይ ምዘና ላይ የሚስተዋሉ የግንዛቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ በመጠቆም።

የትምህርት አመራሩም የተማሪ ክፍል ጥምርታ ችግርን ከመቅረፍ በተጓዳኝ በየደረጃው ያለውን የግንዛቤና የአቅም ውስንነት ለመፍታት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች በትኩረት እንዲሰሩ ማድረግ አለበት ብለዋል ።

በሲምፖዚየሙ ላይ አራት የጥናትና ምርምር ስራዎች የቀረቡ ሲሆን ከዲላ ዩኒቨርሲቲና በክልሉ ከሚገኙ አራት የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች፣ የ1ኛ ደረጃ መምህራንና የትምህርት ዘርፉ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም