አትሌት ብርሃኑ ፀጉ ለአራት ዓመታት ከውድድር ታደገ

566

አዲስ አበባ፣መጋቢት 10/2012 (ኢዜአ) በአበረታች መድሃኒት ተጠርጥሮ ጉዳዩ ላለፉት ሰባት ወራት ሲታይ የቆየው አትሌት ብርሃኑ ፀጉ መድሃኒት መጠቀሙ በመረጋገጡ የአራት ዓመት የውድድር እገዳ ተላለፈበት።

አትሌት ብርሃኑ ፀጉ እ.አ.አ መስከረም 15 ቀን 2019 በዴንማርክ ኮፐንሃገን በተካሄደው የግማሽ ማራቶን የግል ውድድር አምስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው።

ከውድድሩ በኋላ ናሙና ተወስዶ የነበረ ሲሆን በተደረገው ምርመራም ኢፒኦ የተባለ አበረታች መድሃኒት መውሰዱ ተረጋግጧል።

በመሆኑም አትሌቱ ከማንኛውም ውድድር የአራት ዓመት እገዳ ውሳኔ ተላልፎበታል።

አበረታች መድሃኒት ተጠቅሞ ሮጧል በተባለበት የኮፐንሃገን ውድድር ያስመዘገበው ውጤትና ሽልማት የተሰረዘ መሆኑንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ሶስት አትሌቶች በግል በተደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተከለከሉ አበረታች ቅመሞችን እንደወሰዱ በመጠርጠራቸው ጉዳያቸው በመጣራት ላይ እንደሆነም ገልጿል።

በኢትዮጵያ በስፖርተኞች ላይ የሚደረገው ምርመራና ቁጥጥር በብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በኩል ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም ተነግሯል።