ኢንስቲትዩቱ ለመኖ ችግር ሳይንሳዊ መፍትሄ በመስጠት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

61

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10/2012 ( ኢዜአ) ዓለም ዓቀፉ የቁም እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ለመኖ ችግር ሳይንሳዊ መፍትሄ በመስጠት አርብቶ አደሩ በእንስሳት ሃብቱ እንዲጠቀም እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

በተያዘው ዓመት ለ2 ሺህ 500 አርብቶ አደሮች አምስት ሚሊዮን ብር አመላካች የእንስሳት መድህን ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጉንም ገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሃብቷ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት ያልቻለችው በቂ የመኖ አቅርቦት ባለመኖሩ እንደሆነ ነው የገለጹት።

የዘርፉ ተዋንያን በፖሊሲና ስትራቴጂ የታገዘ ሳይንሳዊ የእንስሳት እርባታ አለማካሄድና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ማነስም የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ አድርጓል ይላሉ።

በዓለም ላይ አንድ ቢሊዮን ያህል ሰዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ኑሯቸው ከእንስሳት ሃብት ልማት ጋር የተቆራኘ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ከኢትዮጵያ የመሬት ስፋት 60 በመቶ የሚሆነውም አርብቶ አደሩ የሚኖርበት ነው።

ዘርፉ የምግብ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ለምጣኔ ሃብት ዕድገት፣ ለድህነት ቅነሳና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚጫወተው ሚና ቀላል እንዳልሆነም ተመራማሪዎቹ አንስተዋል።

የኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ዘረመል ተመራማሪ ዶክተር ታደለ ደሴ "ለእንስሳት ልማቱ የሚገባውን ትኩረት አለመስጠታችን አሁን ላለንበት ዝቅተኛ የምርታማነት ደረጃ አድርሶናል " ብለዋል። 

የግብርናውን ዘርፍ ከመሰረቱ ለመለወጥ በሙከራ ደረጃ የተገኙ መልካም ልምዶችና የምርምር ውጤቶችን በፖሊሲ በመደገፍ ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የፖሊሲና የአሰራር ክፍተቶች መኖራቸውን በመጠቆም።

ኢንስቲትዩቱ በችግሩ ላይ ባደረገው ጥናት በተለይ ዝናብ አጠር የአርብቶ አደር አካባቢዎች እንስሳት የሚሞቱት በመኖ እጥረት መሆኑን አረጋግጧል።

ለዚህ ሳይንሳዊ መፍትሄ በመስጠት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን፤ የመኖ አይነቶችንም ከአርብቶ አደሩ ጋር በመገምገም ለአካባቢ ተስማሚ መሆናቸውንና ጥቅማቸውን መረዳታቸውም ተገልጿል።

አርብቶ አደሩ ስለ አጠቃቀማቸው ጭምር መገንዘቡን ያብራሩት በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ተመራማሪ ዶክተር ይሄነው ዘውዴ  በዚህም  በርካታ  ውጤቶች  መገኘታቸውን  ተናግረዋል። 

እንስሳቶች በማድለብ አርሶ አደሩ የተሻለ ገቢ  እንዲያገኝና  ተጠቃሚ  እንዲሆን  መቻሉንም  ገልጸዋል። 

ኢንስቲትዩቱ ከ30 እስከ 50 በመቶ የምርት ብክነት መቀነስ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ማስገባቱንም አክለዋል። 
የአዝርዕትና የእንስሳት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ክንዱ መኮንን በበኩላቸው በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የግጦሽ የመኖ ዝርያ አይነቶች እያስተዋወቅን ነው ብለዋል።  

መንግስትና ሌሎች የልማት ድጋፍ ሰጪ አጋሮች ይህንን መሰረት አድርገው በቂ  በጀትና የሰው ኃይል መድበው ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

አርብቶ አደሩ የግጦሽ መሬትን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠቀም በግጦሽ መሬት አስተዳደር ላይ ያተኮረ ስራ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ተመራማሪዎቹ በአገሪቷ ሰፊ የግጦሽ ቦታዎች ቢኖሩም የአጠቃቀም ስርዓት ባለመኖሩ መሬቱ በአጭር ጊዜ ጉዳት እንደሚደርስበት ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ የኬንያን ልምድ በመቅሰም በተለይ ዝናብ አጠር አካባቢዎች ላይ አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ አመላካች የእንስሳት መድህን ሽፋን ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት ማድረጉንም ገልጸዋል።

በመስከረም 2012 ዓ.ም የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ቦረና አካባቢ ለሚገኙ 2 ሺህ 500 የኢንሹራንስ ፖሊሲ ለገዙ አርብቶ አደሮች የአምስት ሚሊዮን ብር የእንስሳት መድህን ክፍያ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

ይህም የእንስሳቱን ሕይወት በመታደግ አርብቶ አደሩን ከኪሳራ አድኗል ነው ያሉት።

እ.አ.አ ከ1974 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስራውን የጀመረው ዓለም አቀፉ የቁም እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት በእንስሳት አመጋገብና ጤና አጠባበቅ፣ በአርብቶ አደሩ፣ በእሴት ሰንሰለት፣ በመሬት አጠቃቀምና ሌሎችም ዘርፎች ጥናትና ምርምር በማከናወን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም