በደቡብ ወሎ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት አለፈ

115

ደሴ ፤መጋቢት 10/2012(ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በደረሰ የተሸከርካሪ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ14 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።


የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መኮንን ሹሙ ለኢዜአ እደገለጹት አደጋው የደረሰው ትላንት ምሽት 12 ሰዓት ከላሊበላ ወደ ግሸን ማርያም ይጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ወደኋላ ተንሸራቶ ጥልቅ ገደል ውስጥ በመግባቱ ነው።

 የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-02180 አማራ የሆነ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ግሸን ማርያም ለመድረስ አምስት ኪሎ ሜትር ሲቀረው አምባሰል ወረዳ 023 ቀበሌ ኣካባቢ በግምት 150 ሜትር ገደል ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።

 በአደጋውም ተሽከርካሪው ይዟቸው ከነበሩ 29 መንገደኞች መካከል 10 ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ በ14ቱ ላይ ከባድ ቀሪዎች ላይ ደግሞ ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን ተናግረዋል።


ተጎጂዎች ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል የተወሰዱ መሆናቸውን ዋና ኢንስፔክተር መኮንን አደጋው በምሽት መድረሱ የእርዳታ ስራውን አስቸጋሪ ማድረጉን አስረድተዋል።


የአደጋው ዝርዝር ሁኔታ እየተጣራ መሆኑን ጠቁመው የሟቾች አስከሬን ዛሬ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንደሚላክም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም