ሴቶች በመሪነትና በተመራማሪነት ጎልተው እንዲወጡ የማህበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ያስፈልጋል ተባለ

710

መቀሌ ኢዜአ መጋቢት 08/2012 ዓም ሴቶች በመሪነትና በተመራማሪነት ጎልተው እንዲወጡ የማህበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ አሳሰበ ።

የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ኃላፊ ፕሮፌሰር ፎቴን አባይ ይህንን ያሳሰቡት ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለሦስተኛ ጊዜ ባዘጋጀው የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ፣ ሂሳብ  ፣ቢዝነስና አመራር የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሴት ምሁራን  በተሳተፉበት ኮንፈረንስ ላይ ነው።

የዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ ትኩረት ሴት ምሁራን የሰለጠኑበትን የሙያ ዘርፍ ለአገር እድገት መረጋገጥ እንዴት ማዋል እንደሚገባ የሚመክር ነው።

ኮንፈረንሱ ሴት ምሁራንን በምርምርና ጥናት ዘርፎች ባከናወኑዋቸው ስራዎች ዙርያ የተሞክሮ ልውውጥ በማካሄድ ለሃገር እድገት የበለጠ ስራ እንዲያከናውኑ ለማበረታታት መሆኑን ፕሮፌሰር ፎቴን ተናግረዋል ።

”በምርምርና ጥናት ዘርፍ ላይ የሴት ምሁራን ቁጥር በሚፈለግ ደረጃ ላይ አልደረሰም” ያሉት ፕሮፌሰር ፎቴን እንዲህ አይነት አለምአቀፍ መድረክ መዘጋጀት ችግሮቻቸውን በቅንጅት ለመቅረፍ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም መላው ማህበረሰብ ሴቶች በአመራር ሰጭነት፣በተመራማሪነትና በመሪነት እንዲበቁ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊደርግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል ።

ባለፉት ሁለት ዙሮች በተካሔዱ የሴት ሙሁራን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በተፈጠረው መልካም  ግንኙነት ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እንዲሰራ እገዛ እንዳደረገለት ገልፀዋል።

ሴቶች በቢዝነስ፣በትምህርት፣ በአመራርነት የሚያጋጥማቸውን ችግርና በሴቶች ጥቃት መከላከልና የወንዶች ሚና በሚሉና በሌሎች ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ከ15 በላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ።

ሴት ምሁራን እንዲህ አይነት ኮንፈረንስ በራሳቸው ሲያዘጋጁ በስራቸው የበለፀ እንዲነቃቁ ያግዛል ያሉት ደግሞ በመዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር እልፍነሽ ይታገሱ  ናቸው ።

ረዳት ፕሮፌሰሯ እንዳሉት ሴቶች ወደ አመራርነት በማምጣት በኩል ያለው ዘገምተኛ ለውጥ እንዲሻሸል ለሴት ምሁራን እንዲህ አይነት ኮንፈረንስ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አስረድተዋል ።

ሴቶች  በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአመራርነት  የመሳተፍ እድላቸው እየሰፋ ቢሆንም ድጋፍና ክትትል ያስፈልገዋል ሲሉም ረዳት ፕሮፌሰር እልፍነሽ ተናግረዋል።  

በአገርቱ እድሚያቸው ለከፍተኛ ትምህርት ከደረሱ  ሴት ተማሪዎች መካከል የመማር እድል ያገኙት 13 በመቶ ብቻ ናቸው ያሉት ደግሞ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የስትራቴጂክ አመራር ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል  ናቸው። 

የኢትዮጰያ የከፍተኛ ትምህርት እድሜ 70ኛ አመቱ  እየተጠጋ ቢሆንም የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ባለፉት 27 አመታት ብቻ ነው የተሻለ ለውጥ ሊመጣ የቻለው ብለዋል።

የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ  እየተሻሻለ ቢሆንም ሴቶች በተመራማሪነትና በአመራርነት ያላቸው ቦታ በጣም ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

50 በመቶ ሴቶች ያሉባት አገር ሴቶች በአመራርነትና በተመራማሪነት ያለማብቃት ህልውና ይፈታተናል ሲሉም አቶ ደሳለኝ ገልፀዋል።

በኮንፈረንሱ ላይ የአሜሪካና የአውሮፓ ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት ያልተሳተፉ የሌሎች የውጭ አገራት ሴት ምሁራን የላኩት ጥናታዊ ፅሁፎች በዩኒቨርሲቲው አማካይነት ለውይይት እንዲቀርቡ ተደርጓል።