ልዩነት ሳይገድበን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በአንድነት ልንረባረብ ይገባል... ምሁራን

118

ሐዋሳ፤  መጋቢት 08/2012 (ኢዜአ) ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉም በአንድነት ሊረባረብ እንደሚገባ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ተናገሩ፡፡ 

የዕርቅና ሠላም ግንባታ ዘርፍ ተመራማሪና አማካሪ አቶ ጋረደው አሰፋ እንዳሉት በፋይናንስ እጥረት የአባይ ወንዝን ሳናለማ እስካሁን  ብንቆይም ልንጠቀምበት የሚያስችለን ተፈጥሯዊና ሞራላዊ የባለቤትነት መብት አለን፡፡

ይህንን በመጠቀም የሕዳሴውን ግድብ ኢትዮጵያዊያን ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው በመስጠት እየገደቡት ያለና ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እስኪጀምር በጉጉት የሚጠብቁት እንደሆነም ነው የተናገሩት።  

የግብፅና የአሜሪካ መንግስት ተቃርኖ ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደሆነም የጠቀሱት አቶ ጋረደው፤

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጉዳዩን ለድርድር ክፍት በማድረግ በሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ እየተደረገ ያለው ጥረት የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ግብፅ በግድቡ ዙሪያ የያዘችው አቋም ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ባሻገር የቀጠናው ፖለቲካዊ የኃይል ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ ያመዝናል ከሚል ሥጋት የመነጨ እንደሆነ የጠቆሙት አማካሪው፤ ግድቡ ለኢትዮጵያ ምትክ የለሽ የኢኮኖሚ፣ የልማትና የህልውና ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

"ኢትዮጵያዊያን እንደ ሀገር ታላቅ የጋራ የሆነ የከፍታ ታሪክ ያለን ህዝቦች ስለሆንን ይህንን ክብራችንን ለማስጠበቅ በአንድነት መቆም ከሁሉም አካል ይጠበቃል" ያሉት አቶ ጋረደው፤ ምሁራን በፖለቲካ አመለካከት ቢለያዩም  በህዝብ ጥቅም ላይ ግን አንድ መሆን እንደሚገባ  መክረዋል፡፡

የግጭት አፈታት ተመራማሪው ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ በበኩላቸው ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር የተሻለ አቅም እንደሚፈጥርና ከውጭ የሚመጣ ማንኛውንም ተፅዕኖና ፈተና ለመመከት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በመሆኑም  የተለያየ ርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ እሳቤዎች ቢኖሩም  በሀገር ጉዳይ ላይ ግን አንድ መሆን እንደሚገባ በመጠቆም 

መንግስት የያዘውን በፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የመደራደር አቋሙን አፅንቶ ሊያስቀጥል ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም