ህብረተሰቡ ሥጋትን በማስወገድ ከኮሮናቫይረስ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል

49

መጋቢት 8/2012 ( ኢዜአ) ህብረተሰቡ ከፍርሃትና ስጋት ተላቆ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱንና ማህበረሰቡን ከኮሮናቫይረስ መጠበቅ እንደሚገባው ተገለጸ።

የሚመለከታቸው አካላትም ቫይረሱን አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ እንዳለባቸው ተመልክቷል።

እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚወሰዱ የጥንቃቄ ተግባራት መካከል አንዱ ነው።

"ቪዥን ብራይት ኢትዮጵያ" የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት አባላት ዛሬ መነሻቸውን ቦሌ ክፍለ ከተማ በማድረግ በተለምዶ መገናኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎችን እጅ የማስታጠብ ተግባር አከናውነዋል።

በስፍራው የተገኘው ኢዜአ ህብረተሰቡ ከብሽታው ራሱን ለመጠበቅ እያደረገ ስላለው ጥንቃቄ የመዲናዋን ነዋሪዎች አነጋግሯል።

ከሳሪስ አካባቢ የመጣችው ሰብለወንጌል ተስፋዬ በራስ ተነሳሽነት የእጅ ማስታጠብ ተግባር መፈጸም የሚመሰገንና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ እንደሆነ ገልጻለች።

''ህብረተሰቡ ካለበት ስጋት ባሻገር ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን መጠበቅ ይገባዋል'' ብላለች።

ህብረተሰቡ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል መወሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎችና የሚተላለፉ መልዕክቶችን በአግባቡ መተግበር እንዳለበትም ገልጻለች።

ከቦሌ አራብሳ አካባቢ የመጣችው ሀናን አደም በበኩሏ እጅ የማስታጠብ ተግባሩ መልካም እንደሆነና ሰዎች የራሳቸውን ንጽህና መጠበቅ ላይ ትኩረት እንዲያድርጉ የሚያነሳሳ መሆኑን ነው የተናገረቸው።

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የግል ንጽህናን ከመጠበቅ እንደሚጀምር ተናግራ፤ የግል ንጽህናውን በመጠበቅ ከራሱ አልፎ ማህበረሰቡን መጠበቅ እዳለበት አስረድታለች።

መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡ ከኮሮናቫይረስ ራሱን መከላከል እንዲችል ተገቢ መረጃ ማድረስ እንዳለባቸው የገለጸው ደግሞ መሁብ ያሲን ነው።

እጅን የማስታጠቡ ተግባር በሌሎች ቦታዎችም መቀጠል እንዳለበትና ህብረተሰቡ ለኮሮናቫይረስ ብቻ ሳይሆን የራስን ንፅህና መጠበቅ ልምዱና ባህሉ ሊያደርገው እንደሚገባ ገልጿል።

የቪዥን ብራይት ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞቲ ሞረዳ በበኩላቸው "የእጅ ማስታጠብ ተግባሩን ያከናወነው ያለብንን ማህበረሳባዊና አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ነው" ብለዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ሁሉም የሚመለከተው አካል ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚሰሩ ሥራዎችን የማገዝ ኃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል።

በተለይ ህብረተሰቡ ስለ ኮሮናቫይረስ ያለውን ግንዛቤ ከማሳደግ አኳያ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የበጎ አድራጎት ድርጅት አባላትም እጅ ከማስታጠብ ባለፈ የኮሮናቫይረስን መከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም