ጎንደር ዩንቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየሰራ ነው

78

ጎንደር ፣ መጋቢት 8/2012 (ኢዜአ) የጎንደር ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች በመኖሪያ ክፍላቸው ሆነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉበት አሰራር በመተግበር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በበሽታው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በመለየት ህክምና የሚያገኙበት የማቆያ ማእከል ማቋቋሙንም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ግብረ ሃይል በማቋቋም እየሰራ ነው ።

የተቋቋመው ግብረ ሃይል ተማሪዎች በመኖሪያ ክፍላቸው ሆነው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የሚያስችል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በዚህም በሶፍት ኮፒ የተዘጋጁ መጽህፍቶችንና ሞጁሎችን በኢሜይልና ሌሎች መላላኪያ ዘዴዎች በመጠቀም ክፍላቸው ውስጥ ሆነው በማንበብ እውቀትና ክህሎትን ለማዳበር የሚያግዛቸው መሆኑን ገልፀዋል።

በዩኒቨርሲቲው ድህረ ገጽ የተዘጋጁ መጻህፍትና የምርምር ስራዎችን በቀጥታ በማሰራጨት ተማሪዎች በያሉበት ሆነው የተለያዩ የትምህርት ክፍሎችን እንዲከታተሉ የሚያደርግ ነው።

በምግብ አዳራሾች በመመገቢያ ሰዓት የሚስተዋለውን ሰልፍ በመቀነስ የኮሮና በሽታን ለመከላከል አንድ ሰዓት የነበረውን የቁርስ የምሳና የእራት መመገቢያ ሰአት ወደ ሶስት ሰዓት እንዲራዘም ተወስኗል።

ስለ በሽታው መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች እንዲሁም ምልክቱ የታየበት ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ጊቢዎች እየተሰጠ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው ዓለም አቀፍ ገጽታ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ለመቆጣጠር አንድ የህሙማን ማቆያ ማእከል በማቋቋም ወደ ስራ ተገብቷል።

በከተማው በሚገኝ አንድ ጤና ጣቢያ የተቋቋመው ማእከል 30 የህሙማን አልጋዎችና ሌሎች የህክምና መስጫ ክፍሎችን ከማሟላት ባሻገር 18 የህክምና ባለሙያዎች በቋሚነት መመደቡን ተናግረዋል።

ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ተጠርጣሪዎችን በምርመራ ለመለየት እንዲቻል የመመርመሪያ መሳሪያዎች እንዲሟሉለት ለፌደራል ጤና ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በጎንደር ዩንቨርሲቲ በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት በመደበኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ከ25 ሺህ በላይ መደበኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም