ኅብረተሰቡ በአምልኮ ሥነ-ስርዓትም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቱ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

98

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 07/2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሁሉም እምነቶች ተከታዮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ፡፡ 

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ-19/ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ኅብረተሰቡ በአምልኮ ቦታዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።

ጉባኤው አማኞች በቫይረሱ መከሰት ሳይደናገጡና ሳይረበሹ ለፈጣሪያቸው በማደርና በመለመን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበቸውም መክሯል።

ቫይረሱን ለመከላከል ኅብረተሰቡ የግልና የአካባቢ ንጽህና ላይ በማተኮርና የተለመደውን የአኗኗርና የሰላምታ አሰጣጥ ለጊዜው በመተው ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርቧል።

ሕዝቡ የከፋ ስጋት ውስጥ ሳይገባና ቸልተኝነትም ሳያሳይ እርስ በእርስ በመረዳዳት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብሏል ጉባኤው።  

ሁሉም ሰው ፈጣሪን ከሚያስቆጡ ተግባራት በመቆጠብ እንደ የእምነቱ መልካም ተግባራትን እንዲፈጽምም ጉባኤው አመልክቷል።

የኢትዮጵያዊያን አኗኗር ቫይረሱ በቀላሉ እንዲሰራጭ አጋላጭ በመሆኑ ህብረተሰቡ በዚህም እንዲጠነቀቅ ነው ያስገነዘበው።

የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሃሳብ ተረድቶ መፈጸም አስፈላጊ መሆኑም በመግለጫው በአጽንኦት ተመልክቷል።

የንግዱ ማህበረሰብ በሸቀጦች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ከሰብዓዊነት አንጻር የማይገባና በመንፈሳዊ ህይወትም ሀጥያት በመሆኑ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠብ ጉባኤው አሳስቧል።

ቫይረሱን ፈጥኖ ለመቆጣጠር የመንግስት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራና በአገር አቀፍ ደረጃ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርግ የሃይማኖት ጉባኤው ጠይቋል።

በተለያዩ ጉዳዮች የሚካሄዱ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ለቫይረሱ መባባስ አስተዋጽኦ ስለሚኖራቸው መንግስት ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ ያስተላለፈው ውሳኔ ተገቢ መሆኑንም አመልክቷል።

የኮሮና ቫይረስ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ዜጎች ለጉዳት እንዳይጋለጡ ከዛሬ ጀምሮ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሁለት ሳምንት እንዲዘጉና ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ ውሳኔ ተላልፏል።

በእምነት ተቋማት ጭምር ሰዎች ባይሰበሰቡ ተመራጭ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ መግለጻቸው ይታወቃል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም