ለቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መግቢያና ለግለሰብ አስጎብኝዎች የዋጋ ትመና ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ

108

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) ለቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መግቢያና ለግለሰብ አስጎብኝዎች የዋጋ ትመና ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ። 

በዋጋ ትመናው ዙሪያ የባህልንና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ አስጎብኚ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ምክክር ተካሂዷል።

በምክክሩ የመመሪያው አስፈላጊነት፣የተፈጻሚነት ወሰንና ባለድርሻ አካላት ሚና ዙሪያ በሚኒስቴሩ የቱሪዝም መዳረሻ አስተዳደር  ዳይሬክተር አቶ ሁንዴ ከበደ ማብረሪያ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ያለው የመደራሻ ቦታዎች ክፍያ ወጥ ካለመሆኑም በላይ ከሚሰጠው አገልገሎቶች ጋር የማይመጣጠን የዋጋ ጭማሬ በየጊዜው እየተስተዋለ መሆኑ ተነስቷል።  

ይህ ጉዳይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ እንዲቀንስ ከማድረጉም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገጽታ እንዲበላሽ እየደረገ ነው ተብሏል።  

አቶ ሁንዴ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት የዋጋ ትመና መመሪያውን ለማዘጋጀት በአገሪቷ በሚገኙ መዳረሻዎች የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል ያሉት አቶ ሁንዴ የተለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መመሪያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

መመሪያው ጎብኚዎች የሚያነሱትን ቅሬታ ለመፍታት አቅጣጫዎችን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል ነው ብለዋል።   

በፌደራል፣ በክልሎች፣ በግለሰቦችና በኃይማኖት ተቋማት የሚተዳደሩ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ሁንዴ መመሪያው እነዚህን መዳረሻዎች የሚያስተዳሩ አካላት በተናበበ መልኩ እንዲሰሩ እድል የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።  

የመዳራሻ ቦታ ዋጋ ተመን ከመወሰኑ በፊት ያለውን ኃብት፣ የአገልግሎት ስብጥርና ጥራት፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተሞክሮዎች ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባልም ነው ያሉት።  

በመመሪያው መሰረት የዋጋ ትመና ሲወጣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዳደር የሚያስፈልጉ ወጪዎች፣ ለማልማትና ለጥበቃ ምን ያህል ዋጋ ያወጣል? የሚሉ ጉዳዮችም ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል።   

አቶ ሁንዴ እድሚገልጹት በበመሪያው ላይ ግብዓት የማሰባሰብ ስራዎች እየተከናወነ ሲሆን በዚሁ ዓመት ተጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።  

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ከእለት እለት እየጨመሩ መሆኑን ጠቁመው በተደረገው ጥናት በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከሦስት መዳረሻዎች በላይ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።  

''ዋጋ መጨመር ብቻ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዲያመዝን ያደርጋል'' ያሉት አቶ ስለሺ በሚጎበኙ በታዎች ያሉ አገልግሎቶች ከዋጋው ጋር የተጣጣሙ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

የተጋነነ ዋጋ የሚጠዩቁ አካላትን በመንግስት ኃላፊነት በተሰጣቸው አካላት ወደ ማስመር ማስገበት እንደሚገባም በመጠቆም።  

የኢትዮጵያ አስጎብኝዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ያዕቆብ መላኩ በበኩላቸው ከዚህ በፊት በዘፈቀደ የሚወጣ ዋጋ በስራችን ላይ ተጽእኖ ፈጥሮ ነበር ብለዋል።  

''የክልል የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎችና የግል አስጎብኚዎች በፈለጉት ጊዜ በራሳቸው ሰዓት ዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ ያሉት ፕሬዳንቱ ይህም በእኛ ስራ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ ነው፤ ከኛ ጋር በምክክር ዋጋ ሊወጣ ይገባል ባይ ናቸው። 

መመሪያው በአግባቡ ተግባራዊ ከተደረገ አስጎብኚ ድርጅቶችም ሆነ አገሪቷ ተገቢውን ጥቅም የሚያገኙበት ይሆናል ብለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም