የኮሮና ቫይረስ የአፍሪካን እድገት 1 ነጥብ 4 በመቶ በመቀነስ የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት እንደሚጎዳው ተገለፀ

116

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2012 (ኢዜአ) በ2020 በአፍሪካ የተጠበቀው የ3 ነጥብ 2 በመቶ እድገት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ወደ 1 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ እንደሚልና ይህም የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት እንደሚጎዳው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታወቀ። 

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በአህጉሪቱ ሊደርስ የሚችለውን የምጣኔ ሀብት ተጽዕኖ በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ዋና ፀሃፊ ቬራ ሶንግዌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአፍሪካ አህጉር ከተቀረው ዓለም ጋር ይበልጡኑ የተቆራኘች ስለመሆኗ ተናግረዋል።

ለአብነትም በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት እና የአውሮፕላን በረራዎችን ጨምሮ ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች ከተቀረው ዓለም ጋር አህጉሪቷ ትስስር እንዳላት አንስተዋል።

በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በ2020 በአፍሪካ የተጠበቀውን የ3 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ወደ 1 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ በማድረግ በሽታው የአህጉሪቱን እድገት በ1 ነጥብ 4 በመቶ እንደሚቀንሰው ተናግረዋል።

አፍሪካ በቫይረሱ ከተያዙ ሌሎች አገራት አንፃር እስካሁን የዛሬን ሳይጨምር 15 አገራት ብቻ መሆናቸውን እና ይሄም ቁጥሩ ትንሽ ቢሆንም በኢኮኖሚው ላይ ግን ጫና እንደሚያሳድር አንስተዋል።

ይህም በአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር ስለመሆኑ እና የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት እንዲያሽቆለቁል የሚያደርግ መሆኑን አስምረውበታል።

የዓለም የሸቀጦች አቅርቦት ሰንሰለቶች መቋረጥ፣ የፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን በነዳጅ፣ በቱሪዝም እና በውጪ ምንዛሪ ግኝት ረገድ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ገልፀዋል።

በአህጉሪቱ ያለውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማቀዛቀዝ የስራ አጦች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ እና በአፍሪካ ያሉ ነዳጅ አቅራቢ አገራት 65 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ኪሳራ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።

ምግብና የመድሃኒት አቅርቦቶችንም በተመለከተ በሚከሰተው እጥረት ምክንያት የዋጋ ግሽበት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍ ደግሞ ከ10 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያልተጠበቀ ወጪ በአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት ሌላኛው ፈተና ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በሽቀጣ ሸቀጦች ላይ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ግሽበት በአህጉሪቱ ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና እንደሚያስከትል ገልጸው ይህም በአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚያመጣ ተናግረዋል።

ነዳጅ አፍሪካ ወደ ውጪ ከምትልካቸው ምርቶች ዋነኛ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ጸሐፊዋ 7 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ የአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በነዳጅ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀዋል።

የነዳጅ ምርት ወደ ውጪ የሚልኩ የአፍሪካ አገራት በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በ2020 ገቢያቸው ወደ 101 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያሽቆለቁል ከወዲሁ ተገምቷል።

መድሃኒቶችንና የመድሀኒት ቁሳቁሶችን 94 በመቶ ከውጪ  ጥገኛ የሆነችው የአፍሪካ አህጉር ይሄም ትልቁ የምጣኔ ሀብት ፈተና መሆኑን አክለዋል።

በአህጉሪቱ ካሉ 15 አገራት ውጪ ያሉ አብዛኛዎቹ አገራት ምግብ አስመጪ መሆናቸው ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑንም ተመልክተዋል።

በተቻለ መጠን የአፍሪካ መንግስታት ምጣኔ ሀብታቸው እንዳይጎዳ ወጪዎቻቸውን በመቀነስ እና በጀቶችን በመቆጣጠር በኮሮና ሻይረሰ የሚጠበቁ አሉታዊ ተፅእኖዎች ለመቀነስ መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

አህጉሪቱ ውስጥ ወረርሽኝ እንዳይከሰት መድሃኒቶችን ከዋና አቅራቢዎች መግዛት እንደሚጠበቅባቸውም ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል። 

በሴፍቲኔት የምግብ ሽቀጦች አስመጪዎች በፍጥነት መሰረታዊ ምግቦችን ገዝተው እንዲያስገቡ መንግስታት ማበረታት እንደሚኖርባቸው እና አገር ውስጥ በቂ የምግብ ክምችት እንዲኖር ማድረግ ሌላኛው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

የበጀት ማነቃቂያ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣የአፍሪካ ውስጥ ገበያ ትስስርን መጠቀም አንዳንድ አሉታዊ ውጤቶችን ለመቅረፍ ሊያግዝ እንደሚችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም