ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ውድድር በሚያዚያ ወር ይካሄዳል

67

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2012(ኢዜአ) ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ የነበረው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር በሚያዚያ 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ወስኖ ነበር።

ፌዴሬሽኑ ከሁለት ሳምንት በፊት ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ቢገልጽም ምክንያቱን ግን አላሳወቀም ነበር።

በዚሁ መሰረት ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩ ከሚያዚያ 7 እስከ 11 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ በደብዳቤ ማሳወቁን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የተወሰኑ ተሳታፊ አገራት የዝግጅት ጊዜ በቂ ባለመሆኑ ውድድሩ የሚካሄድበት ቀን ይራዘምልን በሚል ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ውድድሩን መራዘሙን ፌዴሬሽኑ በደብዳቤው ላይ አሳውቋል።

የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር (አይ ኤች ኤፍ ቻሌንጅ ትሮፊ) በወንዶች ከ18 እና 20 ዓመት በታች የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው።

በዚህም ለብሔራዊ ቡድኖቹ  ከሶስት ሳምንት በፊት ሙሉጌታ ግርማ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ አማኑኤል ስዩም ምክትል አሰልጣኝ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ተስፋዬ ሙለታ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ ዳንኤል ኃይሉ ምክትል አሰልጣኝ ናቸው።

አሰልጣኞቹ እድሜና ወቅታዊ ብቃትን መሰረት በማድረግ ከእጅ ኳስ ፕሮጀክቶችና ከኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ላይ ተጫዋቾችን መምረጣቸውን ነው አቶ ሞላ የገለጹት።

የልደት የምስክር ወረቀትና ሌሎች ማንነትን የሚገልጹ ሰነዶች በመጠቀም እድሜን ለመለየት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

የተመረጡት ተጫዋቾች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው ጅምናዚየምና በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ልምምድ ማድረግ አንደሚጀምሩም ጠቁመዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ዞን አምስት ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛንያና ኡጋንዳ ይገኛሉ።

የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ውድድር ለታዳጊ አገራት ውድድር መፍጠርን ዓላማ አድርጎ የሚካሄድ እንደሆነ ነው አቶ ሞላ የሚገልጹት።

ከዚህም አንጻር ግብጽ በስፖርቱ የተሻለ ደረጃ ላይ የምትገኝ በመሆኗ በስፖርቱ ያደጉ አገራት ጋር እንድትወዳዳር በመወሰኑ በውድድሩ ላይ እንደማትሳተፍ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድርን በ2006 ዓ.ም ማስተናገዷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም