የትግራይ ክልል ለአዲስ አበባው የቦንብ ጥቃት ተጎጂዎች የ5ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

123
መቀሌ ሰኔ 22/2010 የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም. መስቀል አደባባይ ለሰልፍ በወጡ ንጹሀን ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ የሚሆን 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። የክልሉ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ማንነትን መሰረት አድርገው እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችና በደሎችን እንደሚያወግዝም አስታውቋል። የክልሉ መንግስት ካቢኔ  ዛሬ ተወያይቶ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ማንነትን በመለየት የሚፈጸሙ ጥቃቶች የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብትና ነጻነትን የሚጻረሩ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስትና ክልሎች የዜጎች መብትና ነጻነት ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ጠንክረው እንዲሰሩ ጠይቋል፡፡ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለድጋፍ በወጡ ንጹሃን ላይ የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት በማውገዝ የክልሉ መንግስት ለተጎጂዎቹ ማቋቋሚያ የሚሆን 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑንም በመግለጫው አስታውቋል፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆችን በዘላቂነት ለማቋቋምም የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁሟል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም