ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም ለማስረዳት በተለያዩ አገራት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ላከች

64

መጋቢት 3/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴው ግድብ ላይ ያላትን አቋም ለማስረዳት በተለያዩ አገራት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በመላክ ላይ ትገኛለች።

በዚሁ መሰረት በኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የተመራ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ዛሬ ኬንያ ናይሮቢ በመገኘት ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያላትን ግልጽ አቋም ለፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስረድቷል።

ሁለቱ መሪዎች ክህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ያደረጉትን ውይይት ን ተከትሎም የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራው የልኡካን ቡድን በቀጣይም በሌሎቹ የአባይ ተፋሰስ አገራት ተመሳሳይ ጉብኝት በማደረግ ለአባል አገራቱ መሪዎች የኢትዮጵያን አቋም እንደሚያስረዳ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በቀደሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተመራው ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ከዛሬ ጀምሮ በአውሮፓ በመገኘት ከአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት፣ ከፈረንሳይ እንዲሁም ከሌሎች የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች ጋር በመገናኘት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን አቋም ለማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

በቀጣይም ተመሳሳይ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የልኡካን ቡድን በአሜሪካ እና በሌሎች አገሮች በመዘዋወር ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያላትን ግልጽ አቋም እንደሚያስረዳ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም