በየጤና ተቋማት ለህሙማን የሞራልና የስነልቦና ምክር መሰጠት አለበት...ጤና ሚኒስቴር

113

አዳማ፣ መጋቢት 3/2012(ኢዜአ) በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን የተገልጋይነት እርካታ ለማረጋገጥ ለህሙማን የሞራልና የስነልቦና ምክር መስጠት እንደሚያስፈልግ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማት መልካምና ምስጉን ባለሙያዎችን ለማፍራት ከህክምና 

አገልግሎት በተጨማሪ ለህሙማን የሞራልና የስነልቦና ህክምና መስጠት በሚቻልበት ሂደት ላይ በአዳማ ከተማ 

ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር እየመከረ ይገኛል።

በጤና ሚኒስቴር የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ የፕላስቲክ ቀዶ  ህክምና ባለሙያ ዶክተር አታክልት  ባራክ  እንዳሉት፤  በጤና ተቋማት አዛኝና ሩህሩህ የጤና ባለሙያዎችን በየደረጃው ማፍራት ያስፈልጋል።

በጤና ተቋማት የህብረተሰቡን የተገልጋይነት እርካታ እውን ለማድረግ ታማሚውን ህክምና ከመስጠት ባለፈ 

በሞራልና ስነልቦና ማከም አለብን ብለዋል።

ባለሙያው በክልሎችና በፌዴራል በሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና  ጣቢያዎች የህሙማን አያያዝን የተመለከተ  ጥናት  መካሄዱን ገልፀዋል።

የጥናቱ ዓላማ የውጭ ሀገር ተሞክሮዎችን በማካተት የታካሚውን  ስብዕና በመገንባትና ሞራሉን በመጠበቅ  በተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የሰዎችን ባህሪ ከመለወጥ ጀምሮ የህክምና ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የድርሻቸውን 

እንዲወጡ  ጭምር ጥናቱ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ከህክምና አገልግሎት አሰጣጥ በተጨማሪ በታካሚዎች ስብዕናና ሞራል ህክምና በተመለከተ  የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው የጤና ተቋማት ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ተናግረዋል።

በዋናነት ሙያተኞቹ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሥርዓት እንዲኖራቸው የሚያስችልና የጤና ዘርፍ ፕሮግራሞችን 

ከማሳካት አንፀር ሚናው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለተገልጋይ ከበሬታ ያለውን ሙያተኛ በየደረጃው በሚገኙ የጤና ተቋማት ለማፍራት ታማሚዎች በሽታቸውን  ከማከም ባለፈ ስነልቦናቸውንና አእምሮአቸውን ጭምር መፈወስ መቻል አለብን ያሉት ደግሞ የአለርት  ጠቅላላ

 ሆስፒታል ሥራአስኪያጅ ዶክተር ወንጣሻ ባህሩ ናቸው።

መንፈሳቸውን በማከምና በመንከባከብ ረገድ ሆስፒታላቸው ለህሙማን ሞራልና ስብዕና ግንባታ ላይ የተሻለ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ጥሩ ልምድ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ከተገልጋዩ ህመም  ጀርባ ያሉትን ችግሮች ማከም ስንችል በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን የተገልጋይነት

 እርካታ እውን ማድረግ እንችላለን ነው ያሉት።

በአዳማ ከተማ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከክልሎችና ከፌዴራል የጤና ተቋማት የተወጣጡና የተሻለ

 ተሞክሮ ያላቸው ተቋማት የወከሉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆኖዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም