ለተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማቋቋም ሕብረተሰቡ በቅንጅተ እንዲንቀሳቀስ ተጠየቀ

79
ሶዶ ሰኔ 22/2010 በግጭት የተፈናቀሉትንና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ማህበረሰቡ በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀስ ተጠየቀ፡፡ በሃዋሳና አካባቢው በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ የደረሰውን አደጋ በመቃወም በሶዶ ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍም መልኩን ቀይሮ ወደዘረፋና ንብረት ማውደም በመዞሩ የሰው ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙም ይታወሳል፡፡ የወላይታ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ እታገኘሁ ኃይለማሪያም ትናንት በሰጡት መግለጫ በችግሩ የተከሰተውን ጉዳት ለመቋቋምና አካባቢውን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ ዞኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ ሲሆን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ለማረጋገጥ ያልተቋረጠ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል። "የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት መልሶ ለማቋቋም ዞኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ኮሚቴ በማቋቋም የተደራጀ ሥራ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል፡፡ በሃዋሳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ወገኖች የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ የመለየት ሥራ መሰራቱን ገልጸው፣ በድጋፉ በተለይ ለእናቶችና ህጻናት እንዲሁም ለአቅመ ደካሞች ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡ ዞኑ በምክር ቤት በማስወሰን 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት ኃላፊዋ 1 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተለያዩ ቁሳቁስ መገዛታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከ1 ሺህ በላይ ብርድ ልብስና ሌሎች አልባሳት፣ 3 መቶ ኩንታል ዱቄት፣ ለህጻናትና ለወላድ እናቶች አስፈላጊ የሆኑ የውስጥ ንጽህና መጠበቂያዎችን ጭምር ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ የተለያዩ ረጂ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን የማስተባበር ተግባር የተከናወነ ሲሆን እየተደረገ ያለው ርብርብ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት በተቀናጀ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡ ለእዚህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችና ከአገር ውጭ ያሉ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ገንዘብ ማስገባት የሚችሉበት የባንክ ሒሳብ መከፈቱን ነው ወይዘሮ እታገኘሁ የተናገሩት፡፡ በሶዶ ከተማ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ የመንግስትና የግል ንብረቶች መውደማቸውን አስታውሰው፣ በችግሩ የተፈናቀሉትን ግለሰቦች በዘላቂነት ለማቋቋም በከተማዋ ከንቲባ የሚመራ አደረጃጀት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡ በእስከአሁኑ ሂደትም የወደሙ ንብረቶች ልየታ መደረጉንና በቀጣይም ዜጎቹን ለማቋቋም ወደተግባር ሥራ ውስጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ማህበረሰቡ እየተረጋጋ በመጣበትና መንግስት ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሕብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚለቀቁ አሉባልታዎች ራሱን በመቆጠብ ከጥፋት ይልቅ ልማት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ በተለይ ወጣቱ የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም