የወሣኝ ኩነት ምዝገባ ዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያሥችል ነው -- ሙፈሪያት ካሚል

88

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2012 (ኢዜአ)  የወሣኝ ኩነት ምዝገባ ዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያሥችል መሆኑን የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ፡፡ 

ሚኒስተሯ ይህንን ያሉት አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታትስቲክስ ጥናት 2ኛ ዙር የስትሪንግ ኮሚቴ ምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩም ኢትዮጵያ የወሣኝ ኩነት ምዝገባን ለማካሄድ አለም አቀፍ ስምምነቶችን ተፈራርማ ወደ ስራ መግባቷም ተመልክቷል፡፡

ሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ አለም አቀፍ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የአሰራር መርህን የተከተለ ምዝገባ ለማድረግ የሚያችል የአሰራር ስርዓት አልነበረም፡፡  

ይህም አገሪቷ የገባችውን አለም አቀፍ ስምምነት ከማሟላትና ምዝገባው ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር ከፍተኛ ክፍተት ፈጥሮ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡

''ሆኖም መንግስት ባሳየው ቁርጠኝነት ምዝገባው ከሃምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉን አቀፍ ቀጣይነትና ቋሚ በሆነ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል'' ብለዋል፡፡

ይህ በአገሪቷ እየተካሄደ የሚገኘው የወሣኝ ኩነት ምዝገባም ዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የሚያሥችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገኙ ለማስቻል ምዝገባው ወሣኝነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በየጊዜው የሚወጡ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በተሟላ መረጃ እንዲደገፉ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የሚወጡ ህጎችም ሆኑ ፖሊሲዎች በተገቢው መንገድ ስራ ላይ እንዲውሉ ለማረጋገጥ የምዝገባው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል፡፡

የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል በበኩላቸው በመድረኩ እስከ ተሰሩ ስራዎች ተገምግመው ለቀጣይ ስራዎች ዕቅድ ግብዓት የሚሰባሰብበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ሁሉን አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታቲስቲክስ ጥናቱ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳዳሮች ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የሚካሄድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ጥናቱ አገሪቱ ልታዘጋጅ በዝግጅት ላይ ለምትገኘው የአምስት ዓመት አዲስ የምዝገባ ስትራተጂ እንደ ግብዓት የሚያገለግል ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ 19 ሺህ የሚሆኑ የወሣኝ ኩነት ምዝገባ ጣቢያዎች ቢኖሩም በስራ ላይ የሚገኙት ግን 16 ሺህ 899 ናቸው ተብሏል፡፡

እስከ አሁን በተካሄዱ ምዝገባዎች የልደት ኩነት ምዝገባ 15 በመቶ ላይ ሲገኝ ሌሎቹ ከዚህ በታች መሆናቸውም ታውቋል፡፡

ይህ አገር አቀፍ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና ስታትስቲክስ ጥናት ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ሃምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑም ተመልክቷል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም