በጋምቤላ ክልል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል

871

ጋምቤላ፣ መጋቢት 1/2012( ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ።

”የህፃናት ጋብቻን በማስቆም እኩልነት ላይ የተመሰረተ የተሻለ ዓለም እንፍጠር ” በሚል መሪ ሃሳብ  የዓለም የሴቶች ቀን  በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ አከባበር ስነስርዓት ወቅት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ቶማስ ቱት  እንደገለጹት

በክልሉ ከሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መካከል ያለ እድሜ ጋብቻ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻና  የውርስ ጋብቻ ይገኙበታል።

ድርጊቱ ሴቶችን ለተለያዩ ችግሮች እየዳረጓቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን በማስቀረት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡን ጨምሮ የየሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አጁሉ አቻር በበኩለቸው “በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም የተፈለገው ውጤት ሊመጣ አልቻለም “ብለዋል።

ይህም ችግሩን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡና የሌሎች ባልድርሻ አካላት ተሳትፎ ውስን በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ማህበረሰብ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ ኛጋዋ ፊሊፕ በሰጡት አስተያይት በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ከሚፈጥሩባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጫና በተጨማሪ ለተለያዩ በሽታዎች እየዳረጓቸው  መሆኑን ተናግረዋል።

”ችግርን ለመከላከል የጉዳዩ ባለቤት የሆንን  ሴቶች ግንባር ቀደም ተዋናኝ ልንሆን ይገባል” ብለዋል።

“ወላጆች ሴት ልጆቻውን ካለእድሜ ጋብቻ በመከላከል ትምህርታቸው እንዲከታተሉ መስራት አለባቸው “ያለችው ደግሞ ሌላዋ  ተሳታፊ  ተማሪ ጋሳመን ኡሞድ ናት።