ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ

170

አዲስ አብባ፣ መጋቢት 1/2012 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2012 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ተጨማሪ በጀት እና ሌሎች ተጨማሪ ረቂቅ አዋጆችን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡ 

ምክር ቤቱ በአምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባው 7 የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን ተመልክቷል።

ከአዋጆቹ መካከል የ2012 በጀት አመት የፌደራል መንግስት የተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ ላይ መክሯል።

ረቂቁ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ከገጠመው ችግር የሚላቀቅበትን አማራጭ የያዘ መሆኑ ተመልክቷል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቶታል።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት የልማት ብድርን ከሳዑዲ የልማት ባንክ፣ ከኮሪያ ‘ኤክስፖርት-ኢምፖርት’ ባንክ እንዲሁም ከሳዑዲ የልማት ፈንድ ጋር የተደረጉ ስምምነቶችን ለማስፈጸም የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆችን ለቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ እንዲውለበለብ የሚደነግገውን ረቂቅ አዋጅም ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

በረቂቁ ላይ እንደተመለከተው የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ተፈጻሚነት ወሰን በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅጥር ግቢ የሚውለበለብ ይሆናል።

በፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትና መኖሪያ ቤታቸው ህንጻዎች ላይ፣ በሚኒስቴር እና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑ ተቋማት ህንጻዎች፣ በኢትዮጵያ በተመዘገቡ ንግድ መርከቦች፣ ጀልባዎችና አውሮፕላኖች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተብራርቷል፡፡


የአፍሪካ ህብረት በ50ኛ ዓመት ምስረታ በዓል በተከበረበት ወቅት የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ከአባል አገራቱ ሰንደቅ ዓላማ ጎን እንዲውለበለብ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም