በደሴ ከተማ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ

73
ደሴ ሰኔ 22/2010 ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በደረሰበት የመገልበጥ አደጋ ረዳቱን ጨምሮ በዘጠኝ ሰዎች ላይ የሞት አደጋ መከሰቱን የደሴ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የትራፊክ ፖሊስ ባልደረባ ዋና ሳጅን መስፍን ንጋቱ እንዳስታወቁት ዛሬ ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት ላይ የመገልበጥ አደጋ የደረሰበት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-11597 አ.ማ የሆነ የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ነው። እንደ ዋና ሳጅን መስፍን ገለጻ አደጋው ሊከሰት የቻለው 15 ሰዎችን አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ በደሴ ከተማ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኝና 200 ሜትር ጥልቀት ባለው ገደል ውስጥ መንገድ ስቶ በመግባቱ ነው። በአደጋው የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ወዲያወኑ ሲያልፍ ሾፌሩን ጨምሮ በሌሎች ስምንት ተሳፋሪዎች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት መደረሱን ዋና ሳጅን መስፍን አስታውቀዋል። ጉዳቱ የደረሰባቸው ሰዎችም በደሴ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አስከሬንም ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመላክ አደራሻቸውን የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የአደጋው መንስኤ በቀጣይ የሚጣራ መሆኑን ዋና ሳጅን መስፍን አክለው ገልጸዋል። አሽከርካሪዎች ለትራፊክ አደጋ አጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ ከፍጥነት ወሰን በላይ ባለማሽከርከር በሰውና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ቀድመው መከላከል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም