4311

ደብረ ብርሃን/ ነቀምቴ ኢዜአ የካቲት 30/06/ 2012  መንገዳችን መደመር መድረሻችን ብልጽግና መሆኑን በመገንዘብ ሃገራዊ ለዉጡን ለማስቀጠል እንሰራለን ሲሉ የሰሜን ሸዋ ዞን ሴት አመራሮች ገለፁ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው” በሚል መሪ ቃል በደብረ ብርሀን ከተማ በውይይት ተከብሯል።

የዞኑ ሴቶች ፌደሬሽን ፀሃፊ ወይዘሮ ብዙየ ሽመልስ በውይይቱ እንዳሉት ሃገራዊ ለውጡ ግቡን እንዲመታ የሴቶችን ግንዛቤ በማሳደግ ሚናቸውን እንዲወጡ እየተሰራ ይገኛል።

በተለይም በሴቶች ላይ በማወቅም ይህን ባለማወቅ እየተፈፀሙ ያሉ በደሎች እንዲቆሙ ጠንካራ አንድነት ተፈጥሮ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እየቀነሱ ቢሆንም አሁንም በይፋ በቁጥር ቀላል የማይባልና በቤት ውስጥ የሚደርሱ በደሎች በሚፈለገው ልክ አለመቆሙን ገልፀዋል።

በመሆኑም ሴቶችን የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማሳደግና የመከራከር መብታቸውን በራሳቸው እንዲጠበቅ አቅም ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

አሁን እንደ ሃገር የመጣው ለውጥና የመደመር ፍልስፍና ወደ እውነተኛ ብልፅግና እንዲሸጋገር የበኩላቸውን ሚናም እንደሚወጡ የገለፁት ደግሞ ወይዘሮ ብዙነሽ ወልደአረጋይ ናቸው።

የዞኑ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ገነት ቤተ በግብርናና ከግብርና ውጪ ባሉ የስራ መስኮች የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዞኑ ከ341 ሺህ በላይ ሴቶች ተደራጅተው መብቶቻቸውን ለማስጠበቅና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ሴቶች እራሳቸውን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለማላቀቅ ከሚያደርጉት ጎን ለጎን  ባለፉት ሁለት አመታት በሰላም ግንባታ ያበረከቱትን ጉልህ ሚና በማስቀጠል እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ሴቶች ለሰላምና ደህንነት ሚናቸውን እንዲወጡም ከ36 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የገጠርና የከተማ ሴቶች በሰላም ግንባታና አስፈላጊነት ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የዞኑምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሀኑ ታየ በበኩላቸው የተጀመረውን የለውጥ ምእራፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሴቶች ትልቅ ሃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ።

በየደረጃው ያሉ የሴት አመራሮች መልካም አስተዳደርእንዲሰፍንና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው እንዲጠናከር ባሉት አደረጃጀቶች ሴቶችን ማስተማር ይገባል።

መንግስት የሴቶችን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከመቸውም ግዜ በላይ እየሰራ እንደሆነም አስታውቀዋል።

በዓሉ በተከበረበት ወቅት በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲና በሁለተኛደረጃና በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 12 ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል ።

የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በተከበረው በዓል ላይም 600 የሚደርሱ ከተለያዩ ከወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሴት አመራሮችና ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወለጋ ዩኒቪርስቲ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ትናንት በድምቀት ተከብሯል ።

በአሉ የተከበረው ” የሴቶች ደህንነትና መብት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው ”በሚል መሪ ቃል ነው።

 የዩኒቨርሲቲው የሥርአተ ፆታ ዳይሬክተር ዶክተር አሊማ ጅብሪል  እንደገለፁት በአሉ የሚከበረው የሴቶችን መብት ለማስከበርና ለስልጣን ለማብቃት እጅ ለእጅ ተያይዘን ትግላችንን ለማጠናከር ነው ብለዋል ።

የዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚዳንት ዶክተር በሻቱ ፈረደ በበኩላቸው ሴቶች ያለባቸው የሥራ ጫና ከፍተኛ ቢሆንም ችግሩን ተቋቁመው  መብታቸውን ማስከበርና ለከፍተኛ አመራርነት ለመብቃት መታገል እንዳለባቸው አሳስበዋል ።