ግጭቱ በዘላቂነት ለመፍታት የሲዳማና ወላይታ ወጣቶች የመፍትሄ አካል ሊሆኑ ይገባል

859

ሶዶ ሰኔ 21/2010 በሃዋሳና አካባቢው ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረግ ጥረት የሲዳማና የወላይታ ወጣቶች ዋነኛ የመፍትሄ አካል መሆን እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡

ለግጭቱ ምክንያት የሆኑ አካላትም በአፋጣኝ ለህግ ቀርበው እንዲጠየቁ ተጠይቋል ።

የወላይታ ዞን ወጣቶች ፌዴሬሽን የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ትላንት ውይይት አካሂዷል፡፡

በዞኑ የዳሞት ጋሌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አንድነት ኦልካሶ እንደገለፀችው ተያያዥ ባህልና አኗኗር ባላቸውና ተከባብረውና ተቻችለው በሚኖሩ  ብሄረሰቦች መካከል በተከሰተ የጸጥታ ችግር ለደረሰው የህይወትና ንብረት ጥፋት ምክንያት የሆኑ አካላት ለህግ ሊቀርቡ ይገባል ።

በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ከሟቋቋም ጀምሮ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚከናወኑ ተግባራት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ገልጻለች።

እንደ ወጣት አንድነት ገለጻ የሲዳማም ሆነ የወላይታ ወጣቶች ለችግሩ ዋነኛ የመፍትሄ አካል በመሆን አላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ።

ወጣት ጀማል ሙክታር በበኩሉ የከተማውን ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን በማስተባበር በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም ግንባር ቀደም ሚናውን እንደሚወጣ ገልጿል።

የሲዳማም ሆነ የወላይታ ወጣቶች በድረ-ገጽ ከሚለቀቁ አላስፈላጊና ተአማኒነት በጎደላቸው መረጃዎች ሳይዘናጉ ሳይታለሉ ወጣቱ  ህዝቡን የማስተሳሰር ለችግሩ ዘላቂ መፍተሄ ለማምጣት መስራት እንደሚጠበቅባቸው መክሯል ።

የወላይታ ዞን የወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ሚካኤል ዋዳ እንደገለፀው ተዘዋውሮ መስራትና ሃብት ማፍራት የሁሉም ዜጋ ህገ መንግስታዊ መብት በመሆኑ ወጣቶች ከዚህ መሰል ድርጊት ሊቆጠቡ እንደሚገባ አስገንዝቧል ።

“በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ ተገቢ ያልሆኑ መረጃዎች ህዝቡን ወዳልተፈለገ ተግባር መርተውታል” ያለው ፕሬዝዳንቱ ሆን ብሎ በህዝቡ ውስጥ ችግር በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን የሚሯሯጡ አካላት እንዳሉ ወጣቱ መረዳትና መለየት እንዳለበት ገልጿል ።

በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር በመፍታት እንዲሁም የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋምና ለመካስ በሚደረገው ጥረት ወጣቱ ዋነኛ ተዋናይ መሆን እንደሚገባው አሳስቧል ።

ፌዴሬሽኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በአደረጃጀት እንዲመሩ በማድረግ ተፈናቃዮችን የመደገፍ ስራ መጀመሩን የገለፀው ፕሬዝዳንቱ  በተለይ ለሴቶችና ህጻናት ፈጥነው ሊደርሱ የሚገቡ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን ለአብነት ጠቅሷል ።

በሶዶ ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ከወጣት አደረጃጀቶች የተወጣጡና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ተሳትፈዋል ።