አማራጭ የኃየል ምንጭ ኑሯቸውን ለማሻሻል እንደረዳቸው በምዕራብ ሸዋ አርሶ አደሮች ተናገሩ

አምቦ ሰኔ 21/12010 ባዮ ጋዝ  የተባለው  አማራጭ የኃይል ምንጭ  ኑሯቸውን  ለማሻሻል እየረዳቸው መሆኑን በምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡ በአምቦ ወረዳ የጎሱ ቆራ ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋዬ ዲሪርሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ለረጅም ዓመታት ለምግብ ማብሲያና ሌላም አገልገሎት ማገዶን በመጠቀም በሚወጣው ጭስ ምክንያት የባለቤታቸው ዓይን ለጉዳት ተዳርጓል። ከዚህ ችግር ለመውጣት መንግስት ባደረገላቸው እገዛ ከ2005 ዓ.ም ወዲህ  ባዮ ጋዝ የተበለው አማራጭ የኃየል ምንጭ በመኖሪያ ቤታቸው መገንባት ችለዋል፡፡ የከብቶችን ፍግ ለባዮ ጋዝ ኃይል ማመንጫው በግብኣትነት በመጠቀም ለመብራትና ለምግብ ማብሰያነት አገልግሎት እያዋሉ  ኑሮቸውን ቀላል እንዳደረገላቸው ተናግረዋል፡፡ ከኩራዝ በመላቀቅ ሁለት ልጆቻቸውም በምሽት ብረሀን በማግኘታቸው በርትትው እንዲያጠኑና በቤተሰባቸው ላይ ይደርስ የነበረውን የጤና ችግር እንዳቃለላቸው አመልክተዋል፡፡ " የባዮ ጋዝ አማራጭ የኃየል ምንጭ ክረምት በመጣ ቁጥር ሴቶች ሲያጋጥመን የነበረውን  ችግር አቃሎልናል"  ያሉት ደግሞ በጨሊያ ወረዳ የገልመ ጊዮርጊስ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አባይነሽ ደርቤ ናቸው፡፡ ለኩራዝና ለባትሪ የሚያወጡት ወጪ ቀላል እንዳልሆነ ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዋ  በተለይ የኩራዝ ጭስ ለመተንፈሻ አካልና በአይን ላይ የጤና ችግር  ሲያጋልጣቸው  እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ባዮ ጋዝ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ችግሩ እንደተቃለላቸው ገልጸው ልጆቻቸውም ሌሊት ጭምር ተነስተው በማጥናት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል፡፡ በሊበን ጃዊ ወረዳ የቱሉ ባጆ ቀበሌ አርሶ አደር በርሲሳ ደበሌ በበኩላቸው ባዮ ጋዝ  የኃየል ምንጭ  በተለይ ለገጠሩ ህብረተሰብ ወሳኝ የኃይል አማራጭ እንደሆነ በተግባር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ እንዳሉት ባዮ ጋዝ ለመብራትና ምግብ ለማብሰል እንዲሁም ተረፈ ምርቱ ደግሞ ለማገዶና ለአፈር ማዳበሪያነት እንደሚያገለግል አረጋግጠዋል፡፡ ባገኙት የጥገና ስልጠናም የኃይል ምንጩ መሳሪያ ሲበላሽም ሆነ የጎሮቤቶቻቸውን ለመጠገን ተጨማሪ ወጪ እንደማያወጡም ገልጸዋል፡፡ አማራጭ የኃይል ምንጩ  ኑሮቸውን ቀላል በማድረግ የተሻለ ህይወት ለመምራት እንደረዳቸው ነው አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች የተናገሩት፡፡ በዞኑ ውሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የባዮ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አዱኛ ወዳጆ እንዳመለከቱት 2ሺህ አርሶ አደሮችን የባዮ ጋዝ ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል። ሲሰራ የቆየው ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግረበራ የመነሻ ዓመት ጀምሮ እንደሆነ ጠቁመው እስካሁን በ9 ወረዳዎች ውስጥ 485 አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። እንደ አስተባባሪው ገለፃ አርሶ አደሮች የባዩ ጋዝ ቴክኖሎጂን መጠቀም ከጀመሩ ከ2005 ዓ.ም. መጨረሻ ወዲህ ለምግብ ማብሰያና ለከሰል ምርት ሲባል በደን ሀብቱ ላይ ይደርስ የነበረው ውድመት ለመቀነስ አግዟል። አሁንም በርካታ አርሶ አደሮች በዘርፉ የዳበረ ግንዛቤ ስለሌላቸው ቴክኖሎጂውን በተፈለገው መልኩ ማስፋፋት ላይ ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰዋል። "ችግሩን ለመፍታትም በዞኑ 22 ወረዳዎች አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።   የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ የከብቶች እዳሪና ሌሎችንም ተረፈ ምርቶችን በግብአትነት በመጠቀም እንደሚገነባም  አመላክተዋል። ጽህፈት ቤቱ ከኦሮሚያ ባዮጋዝ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባባር ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም