ለህዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን

802

ነገሌ  የካቲት 27/2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን አጠናከረው እንደሚቀጥሉ በምእራብ ጉጂ ዞን የገላና ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በዞኑ ገላና ወረዳ የቶሬ ከተማ ነዋሪ አቶ በቀለ ኢጆ በሰጡት አስተያየት የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠቀም መብት በውጭ ሀይሎች ጫናና ጣልቃገብነት አይስተጓጎልም ብለዋል፡፡

የግድቡን ግንባታ ለማስፈጸም በሚደረገው ጥረት ባለፉት አመታት በሁለት ዙር የገዙትን ቦንድ በማስታወስ ወደፊትም የህዳሴው ግድብ የሚጠይቀውን የገንዘብም ሆነ የህይወት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያቀረቡት የድጋፍ ጥሪ፤ አንድነት ፣ ወንድማማችነትንና ትብብራችንን የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው የቶሬ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኮረሪማ ሸንቁጤ በበኩላቸው፤ የህዳሴ ግድብ የሚፈልገውን ወቅታዊ ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብታችንን ለመጠቀም መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እናደንቃለን ያሉት አስተያየት ሰጨዋ፤ ከወር ገቢያችን በመቀነስ የጀመርነውን  የህዳሴ ግድብ ግንባታ በግብጽ ተቃውሞና በአሜሪካ መንግሥት ጫና አይደናቀፍም ብለዋል፡፡

የህዳሴውን ግድብ ሰርቶ ለማጠናቀቅ በየደረጃው የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገንዘብ ከማዋጣት ባሻገር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድጋፉን በአንድነት እንዲያሳይ በመቀስቀስና በማስተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል፡፡

ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብቷን ለማስከበር መንግስት የውጭ ጫናና ጣልቃ ገብነትን እንደማይቀበል ያሳየውን አቋም እንደሚደግፉም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ደሜ፤ ግድቡ ለድርድር የሚይቀርብ ኢትዮጵያዊ ጸጋ በመሆኑ መብታችንን ሊከበር ይገባል ብለዋል ።

ለህዳሴ ግድብ የማንንም እርዳታና ብድር ሳንፈልግ እውቀታችንን ፣ ገንዘባችንና ጉልበታችንን በማስተባበር እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን ሲሉ ተናግረዋል ።