በክልሉ ለሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት የዳረጉ ኃይሎችን የማጋለጥ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል—ርዕሰ መስተዳድር ደሴ ዳልኬ

2267

ሀዋሳ ሰኔ21/2010 የህዝቦችን የአብሮነት እሴት በመሸርሸር ለሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት የዳረጉ ኃይሎችን የማጋለጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የደቡብ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ደሴ ዳልኬ ገለጹ፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ላደረሰው ጉዳት በክልሉ መንግስት ስም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ በሀዋሳ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አካባቢውን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ የፌደራልና በየደረጃው ያለው የክልሉ ጸጥታ ኃይል ከህዝቡ ጋር በመስራት  ስራ አብዛኞቹ ስፍራዎች ተረጋግተዋል፡፡

ህዝቦችን በማጋጨትና የአብሮነት እሴቱን በመሸርሸር የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ያደረጉትን ኃይሎችን የማጋለጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ሂደት ህዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በቅንጅት በመስራቱ ውጤት እንደተገኘበት አቶ ደሴ ተናግረዋል፡፡

“በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት የተቀናጀ ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡

“ይሄው ተግባር ዜጎች ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ፣ የወደመባቸው ንብረት እንዲተካና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚያደርግ ነው፤ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕረግራምም ያለው ነው “ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹን የማቋቋሙ ተግባር በመንግስት ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ህዝቡ የጀመረውን የመረዳዳት ባህል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በአጎራባች ክልሎች በተፈጠረ ግጭት በጌዲኦና ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አማሮና ቡርጂ አካባቢ ብዛት ያላቸው ዜጎች በመፈናቀላቸው በቂ ድጋፍና ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸውም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ደሴ እንዳሉት ለዚህም በሁለቱ ክልሎች አመራሮችና በፌደራል መንግስት የሚመራ የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን የመለየትና ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ ይካሄዳል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ችግሮች ውስጥ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ አካላትን ወደ ህግ ለማቅረብ የተቀናጀ ስራ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማትና ገለልተኛ አካላት ወደየአካባቢዎቹ ተንቀሳቅሰው የማጣራት ስራ መጀመራቸውን የጠቀሱት  ርዕሰ መስተዳድሩ የሰላሙ ባለቤት የሆነው ህዝብ ለክልሉ መረጋጋት የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ተገቢው እርዳታ እየቀረበላቸው አይደለም በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ የተፈናቃዮች ቁጥር መብዛትና የተቀናጀ ስርዓት ባለመኖሩ ችግሩ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት ጋር በመተባበር ቅንጅት በመፍጠር በተከናወነው ስራ መሻሻሎች እንዳሉና ዜጎችን ወደ ቄያቸው የመመለስ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ጠቅሰዋልል፡፡

በሃገሪቱ ባለፉት ሶስት ወራት በአዲሱ የለውጥ አመራር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎችን ህዝቡ እንደታገላቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡