በአፋር ክልል ከሰው ዘርና ከድንጋይ መሳሪያ ጋር በተያያዘ አዳዲስ ግኝቶች ተገኙ

111

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26/2012 ዓ.ም ከሰው ዘርና ከድንጋይ መገልገያ መሳሪያ ጋር በተያያዘ በአፋር ክልል አዳዲስ ግኝቶች እውን መሆናቸውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ኦልዶዋን እና አሹሊያን የድንጋይ መገልገያ መሳሪያዎች ከሆሞ ኢሬክተስ የጭንቅላት ቅሪተ አካል ጋር በአፋር ክልል ተገኝተዋል።

ግኝቱ የኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ዶክተር ስለሺ ሰማውና የጎና መካነ ጥናት ፕሮጀክትን የሚመሩት ፕሮፌሰር ዶክተር ማይክል ሮጀርስ ነው።

በጎና የተገኙት የሆሞ ኢሬክተስ የራስ ቅሎች ሁለት ሲሆኑ አንዱ ሙሉ የራስ ቅል

የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዓመታት እድሜ ያስቆጠረ ነው።

ግኝቱ አቶ ኢብራሂም ሃቢብ (አሁን በህይወት የሌሉ) እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ2000 በጎና ዳና አውሎ ተብሎ በሚጠራው ወንዝ የተገኘ ነው።

ሁለተኛው ግኝት በከፊል የራስ ቅል እድሜ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረና ቡሲዲሚ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር 1999 በፕሮፌሰር ኒኮላስ ቶዝ የተገኘ ነው።

ይህ ቅሬተ አካል በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከተገኘው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው።

የራስ ቅሎቹ ሆሞ ኢሬክተስ በመባል በሚታወቀው የቅድመ የሰው ልጅ ዝርያ መደብ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

እነዚህ ቅሬተ አካላት ኦልዶዋን የቅድመ ሰው ዝርያ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን አመታት ጀምሮ ሲጠቀምበት የነበረ የድንጋይ መሳሪያ አይነት ሲሆን ይህም የመጀመሪያ የተረጋገጠ የድንጋይ መሳሪያ ቴክኖሎጂ የተጀመረበት ነው።

ከዛሬ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዓመታት ገደማ በፊት "አሹሊያን" ተብሎ የሚታወቀው እና ሆሞ ኢሬክተስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠርቦ ቅርጽ የያዘ የድንጋይ መጥረቢያ የተጠቀመበት ወቅት ነው።

የአሁኑ ግኝት ሆሞ ኢሬክተስ ሁለቱንም የድንጋይ መገልገያ መሳሪያ አይነቶች በአንድ ጊዜ ሰርቶ ይጠቀም እንደነበር አመላክቷል።

በርካታ ተመራማሪዎች እንደገመቱት አሹሊያን ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን አመታት በፊት ቀደምቱን ኦልዶዋን ሙሉ በሙሉ የተካ አይደለም።

ግኝቱ የጭንቅላት መጠኑ በሌላው የአፍሪካ አገሮች ከተገኙትና ሆሞ ኢሬክተስ በመባል ከሚታወቁት የቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካል አነስተኛ የራስ ቅል ቅሪተ አካል ከተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎች ጋር ተገኝቷል።

የተገኘው የራስ ቅል የአንጎል መጠኑ 590 ሲሲ ሲሆን ቀደም ሲል ከሚታወቁት የሆሞ ኢሬክተስ ቅሪተ አካል በጣም ያነሰ ነው።

ግኝቱን በተመለከተ ዶክተር ስለሺ ሰማው እንዳሉት የጎናው ግኝት ቀደምትነት ያለው ኦልዶዋን የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመታት በፊት ጀምሮ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ የጎናው ግኝት ሆሞ ኢሬክተስ ሁለቱንም የድንጋይ ዘመን ቴክኖሎጂ ጎን ለጎን ለረዥም ዘመናት ይጠቀምበት እንደነበር አመላክቷል።

ዶክተር ስለሺ የጎናው የራስ ቅል በድማኒሲ ሳይት ጆርጅያ ከሚገኙት ጋር መመሳሰሉ ቀድሞ ከአፍሪካ የወጡት የቅድመ ሰው ዝርያዎች አንድ ቦታ ሳይቀመጡ እንደገና ወደ አፍሪካ ተመልሰው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ፕሮፌሰር ዶክተር ማይክል ሮጀርስ "አንድ የሆሚኒድ ዝርያ የተወሰነ የድንጋይ ቴክኖሎጂ ሲጠቀም ኖሯል ለማለት ከአሁን በኋላ አስቸጋሪ በሆኑ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ እድገት ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልገው ጥናታችን ያሳያል" ብለዋል።

የጥናትና ምርምር ግኝቶቹ ትላንት "ሳይንስ አድቫንስ" በተሰኘው የኦንላይን መረጃ ምንጭ ይፋ መደረጉን መግለጫው ጠቁሟል።

የጎና የፓሊዎ አንትሮፖሎጂ ጥናት ፕሮጀክት ባለፉት 30 ዓመታት የምርምር ስራው በአለም ጥንታዊና 2 ነጥብ 6 ሚለዮን አመታት ያስቆጠሩ የድንጋይ መሳሪያዎችንና 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን አመታት ያስቆጠረውን አርዲፒተከስ ራሚደስ የተባለውን ጥንታዊ የሰው ዘር ቅሪተ አካል በማግኘት በተለያዩ አለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናሎች ላይ አሳትሟል።

በአሁኑ ወቅትም በፕሮጀክቱ የጥናት ቦታዎች ውስጥ በሚገኙ 6 ሚሊዮን አመታት እድሜ ባላቸው የጥንታዊ አለት/አፈር ንብብሮች ውስጥ ጥናት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም