በአገሪቷ አዲስ የአንድነትና የፍቅር ዘመን መጥቷልና በአግባቡ መጠቀም ይገባናል - ሼህ ሳህለዲን ወዚር

46
አዲስ አበባ ሰኔ21/2010 በአገሪቱ አዲስ የአንድነትና የፍቅር ዘመን መጥቷልና በአግባቡ መጠቀም ይገባናል ሲሉ በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዳያስፖራ ዳይሬክተር ሼህ ሳህለዲን ወዚር አሳሰቡ። ኑሯቸው በአሜሪካ የሆነው ሼህ ሳህለዲን በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ውጭ ሂደው የሚያወያዩበትን ቀንም በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን ነው የገለጹት። በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሼሁ በአገሪቷ ያለው "የለውጥ ንፋስ" ተስፋ ሰጪና ታይቶ የማይታወቅ ሊባል የሚችል መልክ ያለው ነው ብለዋል። ለዚህም ባሳለፍነው ሰኔ 16 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ላመጡት ለውጥ እውቅና ለመስጠት ለመደገፍ በተዘጋጀ ሰልፍ እሳቸውም በአጋጣሚ አገር ውስጥ በመሆናቸው የተሳተፉበት መሆኑን ጠቅሰዋል። በሰልፉ ላይ ያለው የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመተባበርና ሁሉንም ልዩነት ወደ ጎን ትተው ለአንድ አላማ የመቆሙ ጉዳይ የሚያስደስትና ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል። በሰልፉ ማጠናቀቂያ ላይ የተከሰተው የቦንብ ፍንዳታ ደግሞ ከዚህ አስደሳች ታሪካዊ እድል በተቃራኒ የቆመ የሚወገዝ ተግባር መሆኑንም ሼሁ ተናግረዋል። በዚህም አሁን አገሪቱ ውስጥ ያለውን የፍቅርና የአንድነት እንቅስቃሴ የተሳካ እንዲሆን "በፊት ጠፍንጎ የያዘንን ዘረኝነትና ጥላቻ ማስወገድ ተገቢ መሆኑን" መልዕክት አስተላልፈዋል። ይህ እንዲሆንም ሁላችን ባለንበት ፍቅር፣ መከባበርን፣ መረዳዳትንና መተባበርን በተግባር ማሳየት ይገባል ብለዋል። ከዚህ ሌላ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአገር ቤት ባለው ለውጥ ትልቅ ደስታ እንዳለውና የዚህ ለውጥ መንስዔ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ወደዚያ የሚሄድበት ቀን በጉጉት እየተጠበቀ ነው ብለዋል። "ወደ ስፍራው ሲሄዱም ደማቅ አቀባበል ለማድረግ አብዛኛው ሰው ዝግጁ ነው" ያሉት ሼሁ፤ በዳያስፖራው በኩል ያለውን ከሳቸው ጋር ተገናኝቶ የመወያየት ፍላጎት ለሚመለከተው አካል አቅርበናልም ብለዋል። ዳያስፖራው ለአገሩ ሰላምና እድገት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ያለው ተነሳሽነትም ትልቅ መሆኑን ነው የገለጹት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መጥተው በሰላምና በፍቅር አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም