ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ውድድር ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

77

ኢዜአ የካቲት 24/2012  ኢትዮጵያ የምታስተናግደው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድር /አይ ኤች ኤፍ ቻሌንጅ ትሮፒ/ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ።

ዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ወስኖ ነበር።

ነገር ግን ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን በደብዳቤ ማሳወቁን የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቀዋል።

ፌዴሬሽኑ በዚሁ ደብዳቤው በቀጣይ ውድድሩ የሚካሄድበትን ጊዜ እንደሚያሳውቅ መግለጹን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውድድር እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በኅዳር 2012 ዓ.ም እንደነበርና የሜዳዎችን ዝግጅትና ተሳታፊዎችን የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ምርጫ መከናወኑን አውስተዋል።

የፌዴሬሽኑ የልዑካን ቡድንም ኢትዮጵያ ለውድድሩ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ከየካቲት 9 እስከ 12 ቀን 2012 ዓ.ም መጥቶ መገምገሙንና ''በጥሩ ደረጃ ይገኛል'' መባሉንም አስታውሰዋል።

ውድድሩ በወንዶች ከ18 እና 20 ዓመት በታች የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፉበታል።

ኢትዮጵያም የብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኞች ከ15 ቀናት በፊት የመረጠች ሲሆን፣ ሙሉጌታ ግርማ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ አማኑኤል ስዩም ምክትል አሰልጣኝ ሆነው ተመርጠዋል።

ተስፋዬ ሙለታ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ ዳንኤል ኃይሉ ምክትል አሰልጣኝ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ በውድድሩ ይካፈላሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች እጅ ኳስ ውድድርን በ2006 ዓ.ም ማስተናገዷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም