ኢትዮጵያ በራሷ ንብረት በሌላ ኃይል ተጽዕኖ የምትፈርመው ምንም አይነት ስምምነት አይኖርም

1468

አዲስ አበባ፤ የካቲት 24/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በራሷ ንብረት በሌላ ኃይል ተጽዕኖ ተገዳ የምትፈርመው ምንም አይነት ስምምነት እንደማይኖር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አስታወቀ።

ተደራዳሪ ቡድኑ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት እየተደረገ ስላለው ድርድር ሁኔታ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ሰጥቷል።


ግድቡ ለኢትዮጵያ ህልውና አስፈላጊ መሆኑንና አገሪቷ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ በመንግስትና በህዝብ ታምኖበት ወደ ስራ መገባቱም ተገልጿል።


ያም ሆኖ የአባይ ወንዝ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በማይጎዳ መልኩ መገንባቱ ታምኖበት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከግብጽና ከሱዳን ጋር ውይይት ና ድርድር ሲካሄድ ቆይቷል።


በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን ልዩነት ለማቀራረብ አሜሪካ ሶስቱን አገራት እያወያየች ትገኛለች።


ይሁንና አሜሪካ በድርድሩ አዎንታዊ ሚና የተጫወተችባቸው የድርድር ሂደቶች ቢኖሩም አሁን ከአወያይነት ይልቅ እንደ መንግስት አቋም ወስዳ የመጣባችበት ሂደት ትክክል እንዳልሆነ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የግድቡ ግንባታ ሂደት በኢትዮጵያ የግዛት ክልል በኢትዮጵያዊያን ተጀምሮ በኢትዮጵያዊያን የሚያልቅ ሀብትና ንብረት እንደሆነ ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ ህዝቦቿን ከድህነት ለማላቀቅ እየገነባችው ያለው ግድብ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በማይጎዳ መልኩ እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።


ሱዳን በመሪም ሆነ በአገር ደረጃ ግድቡ ይጠቅመናል የሚል ጠንካራ አቋም እንዳላት የገለፁት አቶ ገዱ፤ ግብጽ እንጂ ሱዳን የአባይን ውሃ የመቆጣጠር ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።


ባለፉት አምስት ወራት በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው ድርድር ሰፊ ልዩነቶችን ለማቀረራብ መቻሉን ያነሱት ሚኒስትሩ ከቴክኒክና ከህግ አኳያ በአገራቱ መካከል ልዩነቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።


ኢትዮጵያ በድርድሩ ብሔራዊ ጥቅሟን በሚያስጠብቅ መልኩ እየሄደች እንዳለችና በግብጽና በአሜሪካ በኩል ስምምነቱ በቶሎ እንዲያልቅ ፍላጎት ስለመኖሩም ተናግረዋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ስምምነቱ በጥድፊያ መሆን እንደሌለበትና ድርድሩም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እንደምታምን ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ በራሷ ንብረት በሌላ ተጽዕኖ ተገዳ የምትፈርመው ምንም አይነት ስምምነት እንደማይኖርም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ ያስታወቁት።


አሜሪካ በግድቡ ዙሪያ የያዘችው አቋም በዲፕሎማሲ ውይይት የምትታሰብ አገር እንደመሆኗ በቅርቡ ከእሷ የማይጠበቅ መግለጫ ማውጣቷን ጠቅሰው የያዘችውን አቋም ታርማለች ብለው እንደሚያምኑም አክለዋል።


የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ደግሞ ኢትዮጵያ 86 በመቶ የአባይ ወንዝ አመንጪ አገር እንደመሆኗ ከውሃው ተጠቃሚ መሆን አለባት ብለዋል።


ሉዓላዊ አገር መሆኗንና በሀብቷ ተጠቃሚነት ዙሪያ ሊጋፋ የሚችል ሃይል ሊኖር እንደማይገባም አንስተዋል።


በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ የጋራ ተጠቃሚነትን ያማከለና በታችኛው ተፋሰስ አገራት ጉልህ ተጽዕኖ የማያመጣ መሆኑን ተረድታ እየሰራች ስለመሆኑ ተናግረዋል።