ኢትዮጵያና ኤርትራ በጋራ ለማደግ ጽኑ ፍላጎት ማሳየታቸው ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ጠንካራ ትስስር የሚፈጥር ነው-ነዋሪዎች

74
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ በፍቅርና በጋራ ለማደግ  ጽኑ ፍላጎት ማሳየታቸው ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ጠንካራ ትስስር የሚፈጥር  ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ ። የኤርትራ የልዑካን ቡድን ወደ መዲናዋ መግባቱን ተከትሎ  ኢዜአ  ኢዜአ ካነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ገበየው ዳምጠው እንዳለው ሁለቱ ሀገራት በሰላምና ፍቅር ተሳስረው በጋራ ለማደግ የሰነቁት ራዕይ ለፍጻሜ እንዲበቃ ፍላጎትም ጉጉትም አድሮበታል፡፡ አቶ  ብርሃኑ እሸቱ የተባሉ ሌላው አስተያየት ሰጪም  የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ የተጋባና የተዋለደም መሆኑን ገልጸው በህዝቦች መካከል “የእነሱና የዕኛ” የሚባል ነገር አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ አሁን የተፈጠረው እድል ለፍሬ በቅቶ "ተነፋፍቆ" የቆየው ህዝብ እንዲገናኝ የሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ከመንግሥታቸው ጎን ተሰልፈው ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ጎሹ የተባሉ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት ደግሞ ከፍቅር እጂ ከጸብ የሚገኝ ነገር ባለመኖሩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሻሻል የተጀመረውን ስራ አድንቀዋል፡፡ ወጣት ህይወት ተካም የተጀመረው እርቅ ለፍሬ በቅቶ “እውነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ከጀመረ እኔ ነኝ በመጀመሪያ ሄጄ ወንድም እህቶችን የማቅፈው” የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የኤርትራ የልዑካን ቡድን ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ዛሬ ወደ ሀገሩ ይመለሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም