የአድዋ ስንኞች

969

አየለ ያረጋል ( ከኢዜአ)

“ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፤

እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም”

በአድዋ ድል ክብረ በዓል ወጣቶች በየፊናቸው ተሰባስበው የሚያዜሙት ግጥም ነው። ረቂቋን የአድዋን ድል በተመለከተ ከሚሞዘቁ እስከ ሚነበነቡ ተወዳጅ ስንኞች አሉ። ወደ ስንኞች ከመግባቴ በፊት ግን ጥቂት ‘ስለአድዋ ምን ተባለ’ የሚለውን ‘አባይን በጭልፋ’ እንዲሉ ጥቂት ላውሳ!

የአሜሪካው ሞርጋን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ጌታቸው መታፈሪያ የአድዋ ድል ሁለት መልዕክቶችን አብስሯል ባይ ናቸው። አንድም ቅኝ ገዥዎች ኃያልነታቸው በአፍሪካዊያን እንደሚፈተን የተገነዘቡበት፤ ሁለትም የአፍሪካ ዳያስፖራዎች የተስፋ ስንቅ የታጠቁበት ነው ይላሉ። ባርነት፣ ጭቆና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብዝበዛዎች እልባት እንዲያገኙ ደወል አቃጭሏል ነው መልዕክቱ። ተመራማሪው ያክላሉ “ልክ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያዊያንን ካለአንዳች ልዩነት አሰባስበው ጠላትን ድል እንደነሱት ሁሉ አርቆ አሳቢ አመራር ካለ አፍሪካዊያን እኩልነት፣ ፍትሕና የህልም እንጀራ የሆነባቸውን ሁለንተናዊ አህጉራዊ ሠላም ማግኘት እንደሚችል ወኔ ቆሰቆሰባቸው” ብለዋል።

ዕውቁ አፍቃሪ ኢትዮጵያዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “የአድዋ ድል ዜና በአውሮጳ ኃያላን ዘንድ የጦር አደጋ ጋረጠ፤ ሮምን በመሰሉ የአውሮጳ ከተሞች የፖለቲካዊ ቀውስ ምጽዓት ቀረበ፤ የእንግሊዛዊያንን ሸውራራ እሳቤም በአንድ ሌሊት ቀየረ” ይላሉ።

የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ሃሮልድ ማርክስ በበኩላቸው አድዋ ዳግማዊ ምኒልክ አሮጌውን የሰለሞናዊ መንግስት ለማዋቀር ስትራቴጂያዊ የስኬት ጥግ ያደርጉታል። ለጥቁር ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያ ድል ጮራ የወቅቱ ክብርና ለነጋቸው የይቻላል መንፈስ ያስታጠቃቸው ልዩ ክስተት ሆነም ይላሉ። ምዕራባዊያኑ በጥቁሮች ላይ ለዘመናት ያሳደሩት ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ንቀት እንደነበር ያወሱና የአድዋ ክስተት ቀድሞውንም ኢትዮጵያ በካህኑ ዮሐንስ አገርና ቀደምት የክርስቲያን አገር እንደሆነች በየዘመናቱ የራሳቸው ተጓዦች የዘገቡትን ‘ሚቶሎጂ’ ወይም ታሪክ ዳግም እንዲያሰላሰሉ ማድረጉን ይጠቅሳሉ። በፕሮፌሰሩ ጥናት አንዳንዶች ጫማና ቦላሌ ሳይለብሱ ስልጡን ዜጎች አድርገው ሲመለከቱ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሰለጠኑ አገራት በላይ ራሳቸውን የሚቆልሉ ግብዞች አድርገው ስለዋቸዋል ይላሉ።

በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚ የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ሞዛይክ ብትሆንም ዜጎቿ በአንድ ላይ በጋርዮሽ ታሪክ መጣበቃቸውን ይገልጹና፤ ከነዚህም መካከል አድዋን ልዕለ አውራጃዊ ምልከታ፣ ልዕለ ዘውግ አስተሳስብ የታየበት የጋራ ነጻነት ዓርማ ያደርጉታል። በዚህ ሃሳብ ኢትዮጵያዊው የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ዴሌቦም ይስማማሉ፤ ፕሮፌሰር ላጲሶ አድዋን ኢምፔሪያሊዝምን ያሸነፈ ድል ሲሉም ይገልጹታል።

የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ሬሞንድ ጆናስ ‘የአድዋ ጦርነት’ በተሰኘው መፅሀፋቸው አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት የአድዋን ድል ለማንኳሰስ ቢሞክሩም ሙከራው ወንዝ እንዳላሻገራቸው ይጠቅሳሉ። ‘ታሪክ የተለየ ክስተትን ይወዳል’ የሚሉት ፕሮፌሰሩ አድዋ ተለምዷዊ ጉዞ የቀየሰ፣ ነባር ንግርን የለወጠ፣ ለቅኝ ተገዥዎች የራስ መተማመን ጉልበት ያጎናጸፈ፣ በአጠቃላይ አድዋን የታሪክ ዑደትን የጨዋታ ሕግ የቀየረ ዕውነታ አድርገውታል።

አድዋን ልዩ የሚያደርገው በአንዲት አፍሪካዊት አገር የአውሮጳዊ ኃያል መንግስት እጅ መስጠቱ አይደለም የሚሉት የካናዳው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ምሁር ዶክተር ሜማይሬ ሜናሴማይ፤ ይልቁንስ የማይቻል መሰል እውነት በገሃድ የታየበት ሁነት ነው፤ አዲስ ፖለቲካዊ ተጠየቅ የፈለቀበት፤ ታሪካዊ አድማስ የተከፈተበትም ዕለት ያደርጉታል። በፈላስፋው እምነት አድዋ በታሪክ ኢትዮጵያዊያን ብሔር፣ ጾታ፣ ሃይማኖት፣ ማህበራዊ መደብ ሳይሉና ምንም ልዩነት እንደሌለባቸው በአንድ ማንነት ድርና ማግ ሆነው የዘመቱበት ውስጣዊ ነጻነት፣ ዘመናዊነትና አንድነትን ያረጋገጡበት አድርገውታል። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መላውን ኢትዮጵያን ክተት ብለው በአድዋ እንዳደረጉት ታሪካዊ ድል የአፄ ኃይለስላሴ ‘ዘገምተኛው አብዮት’፣ የደርግ ‘ህብረተሰባዊነት’ እና የኢህአዴግ ‘የዘውግ ፌዴራሊዝም’ መንግስታዊ ስርዓታት ማሰባሰብና ፖለቲካዊ አንድነት መፍጠር አልቻሉበትም በማለት የአድዋን ከፍታ ይጠቅሱታል።

በሌላ በኩል ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕልና አወቃቀር በስፋት ያጠኑት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሊቨን /የታላቋ ኢትዮጵያ መጽሐፍ ደራሲ/ ሁሉንም ነገዶች ያሰባሰበው የአድዋ ዘመቻ ፍሬው ለኢትዮጵያዊያን ብቻ አለመሆኑን ጽፈዋል። ይልቁንም የሚሊዮን ጥቁሮች የኩራትና ወኔ ፏፏቴ ቅርስ አድርገውታል። አድዋ ለጥቁሮች መብት ታጋዩ ማርክስ ጋርቬይ “ኢትዮጵያ እውነተኛዋ የአባቶቻችን ምድር” በማለት ለ‘የምልሰተ አፍሪካ ንቅናቄ’ ቅስቀሳው ተጠቅሞበታል። እውቅ የጥቁር መብት ተሟጋቾች የሃይቲው ቤንቶ ሲልቫን፣ የምዕራብ ኢንዲያኖች ጆሴፍ ቪታሌን፣ እንዲሁም ቡከር ዋሽንግተን፣ ኢዳ ዌልስ፣ ዲ ቦይስ ‘የጺዮን ንጉስ’ ምልክት በማድረግ ለፀረ ቅኝ ግዛትና ዘረኝነት ትግል ቀስቅሰውበታል። በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ከነበሩ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገራት የነጻነት ታጋዮች መካከልም የናይጄሪያው ናምዲ አዝኪዌ፣ የጋናው ክዋሜ ንኩርማን፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ የጀማይካው ጆርጅ ፓድሞሬ በአድዋ ድል ዜጎቻቸውን በመቀስቀስና ከጎናቸው በማሳለፍ፣ ተከታዮችን አፍርተዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናትም አድዋ ከትግል ባሻገር በደቡብ አፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚል ሃይማኖት እንቅስቃሴ ያስጀመረ ታሪካዊ ከስተትም ነው። በአድዋ ድል ማግስት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ ስም አያሌ አብያተ- ክርስቲያናት ታንጸዋል። ለአብነትም የተባበሩት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን፣  የኢትዮጵያ ተልዕኮ በደቡብ አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ፣ የቅዱስ ፍሊፕ ቤተ ክርስቲያን  በደቡብ አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ የምህላ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ሰብዓ-ገነት የእግዚአብሄር መመስገኛ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚሉት ይገኙበታል። ከአፍሪካዊያን አልፎም ጃፓን በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ከሩሲያ ነጻ ለመውጣት አደዋን መነሻ እንዳደረገች የታሪክ ድርሳናት ዘግበዋል።

አድዋ በኢትዮጵያ ታሪክ ፀሀፍትም ሆነ በዘመናዊ የታሪክ ሊቃውንት ዘንድ በብዙ ተተንትኗል።  ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ወልደአረጋይ፣ ነጋድራስ /ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደስልሴ፣ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴና ሌሎች ታሪክ ፀሐፍት ስለ አድዋ ጦርነት ሂደትና ድህረ አድዋ ውጤቶች ብዙ ብለዋል።

አድዋ በየዘመኑ በአሳሾችም ሆነ በአሜሪካና አውሮጳ ጋዜጦች ተነግሮለታል። በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በአድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፣ መትረየሶች አሽካክተዋል፣ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፣ ጎራዴ ተመዟል፣ ጦር ተሰብቋል! ምን አለፋን በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል። የአድዋ ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነጸብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ተዘርዝሮ አያልቅም፤ በአድዋ ጦርነት የተመዘገቡ የይቅርታ፣ የፍቅርና የርህራሄ እሴቶች ከጥቁር ሕዝቦች ድልነት አሻግረው ለእያንዳንዱ ሰው ድል አድርገውታል።

በጥቅሉ በሰው ልጆች ታሪክ አድዋ በዓለም ላይ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተበት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። የአድዋ ድል አሻራ ከኢትዮጵያ አልፎ የዛሬይቱ አፍሪካ ላይም በጉልህ ታትሟል። ይህን ታላቅ የታሪክ ክስተት የኪነ-ጥበብ ሰዎች በየመክሊቶቻቸው፣ የታሪክ ሊቃውንትም በጥናቶቻቸው አውስተውታል። አድዋን ጽምጻዊያኑ እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ እና ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ በዜማዎቻቸ፣ እነ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በፊልማቸው፣ እነ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት በተውኔታቸው፣ ጸጋዬ ገብረመድህንና መሰሎቹ በቅኔያቸው፣ ሌሎችም እንደ መክሊቶቻቸው በኪነ-ጥበብ ለመግለጽ የበኩላቸውን ጥረዋል። ከድሉ ዘመን ጀምሮ በተለይም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በርካታ መወድሶችን/ቅኔዎችን እንደተቀኙ ይነገራል። ዳሩ ግን በየትኛውም የኪነ-ጥበብ መስክ በአድዋ ከፍታ ልክ የተሰራው ስራ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

በዛሬው ጽሁፌ ግን ዘንድሮ 124ኛ ዓመቱን ላስቆጠረው የአድዋ ድል ላይ ከተገጠሙ ስንኞች መካከል በጥቂቱ ማውሳት ወደድኩ!!

ደራሲና ጋዜጠኛ ነብይ መኮነን ‘ስውር ስፌት’ በተሰኘ የግጥም መድብሉ የአድዋን ድል ሲያመሰጥረው አድዋን ‘በደም ግብርነት’ ይገልጸዋል፤ ታሪኩንም ላጥፋህ ቢሉት የማይጠፋ ሕያው ቀንዲል አድርጎታል።

“አድዋ የደም ግብር ነው፤ አበው የለኮሱት ቀንዲል

አድዋ የአፍሪካ ዱካ ነው፤ አበሽ የከተበው ፊደል

ላጥፋህ ቢሉት መች ይጠፋል፤ ጠላት በልቶ ያፈራ ተክል

ለዛሬም ታሪክ ነው፣ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ ለሚል…”

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ምሁር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰይፉ መታፈሪያ “የተስፋ እግር ብረት”  መጽሐፍ “የድል በዓል ማለዳ” በሚል ርዕስ የአድዋን ድባብ ከማለዳው ምናባዊ ትዕይንት ጀምሮ ይቃኛል።

የባንዴራዎቹ ጭብጨባ፤ የቀለማቱ አበባ

እየተራገበ በየካቲት ነፋስ፤ ያተራግቦት፣ ቀስበቀስ

የልቤን ብብት ነክቶኝ፤ የእንክትክት ሣቁን አሣቀኝ።

በሚል የሰንደቁን መውለብለብ፣ የሕብረ ቀለሙን ድምቀት ከልክ በላይ ውስጥን ኮርኩሮ የሚያስፈግግ ሐሴት እንዳለው በዘይቤያዊ ቃላት ገልፆታል። ገጣሚው በቅኔው የሠራዊቱን ቆራጥነት፣ በወኔ በደም ሲቅላላ፣ የመድፍ አረር ያፋጭ ይስለዋል። በስሜት ስካር አድዋ ደፍርሶ በስዕለ ህሌናው የነበረውን የጦርነቱ ማለዳዊ ድባብም እንዲህ ያብራራዋል።

…ዐይነ-ልቦናዬ ዐጽም ያያል

የድል ሜዳውን ይቃኛል።

ባድዋ ድል በዓሉ ማለዳ

የበዓል መድፍ ሲንዱዋዱዋ

(ዱዋ ዱዋ ዱዋ ዱዋ!)

ከሞት እንቅልፍ ተቀስቅሶ

ያ-ዐጽም ዙርያውን ደባብሶ

ጉሮሮውን ጠረገ

እህህህህ! እህህህህ!… እያለ ይቀጥላል።

በአድዋ ኮረብታማ ተራሮች የተኙ ጀግኖችን በሕይወት ተኝተው የሚያንኮራፉ አስመስሎም አቅርቧቸዋል።

…ድንጋ ተንተርሶ፤  አፈር ቅጠሉን ለብሶ።

ከዚያን ያንኮራፋል፤ እንደዚሁም በቅብልብል

የወደቀበቱ ሜዳው፣ ተረተሩ፤

ቀን የማይለውጠው ምስክሩ

የዚያ ጀግና፣ የዚያ ኩሩ።

ስለ አድዋ ከተጻፉ ግጥሞች በስፋት ዕውቅናና አድናቆት የሚቸረው የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ‘እሳት ወይ አበባ’ ግጥም መድብል ውስጥ የሚገኘው ‘አድዋ’ የተሰኘው ግጥም ነው። ገጣሚው በቅኔው አድዋን መልክዓ ምድራዊና ሃሳባዊ ወሰኗን አድማስ ተሻጋሪ፣ ሰማይ ታካኪ፣ ታሪካዊ ስፍራዋ የአጽም ርስትና የደም ትቢያ የተሸበለለባት መቀነት አድርጎ መስሏታል። በዚህች ታሪካዊ ስፍራ በተከፈለው መስዋዕትነት ከባርነትና ነጻነት ስርየትን ሲያጎናጽፍ፣ የኩራት ቅርስ መሆኗንም ሰፊውን ታሪክ በጥቂት ስንኞች እንዲህ ቋጥሯታል።  

አድዋ ሩቅዋ

የዓለት ምሰሶ የአድማስ ጥግዋ፣

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ…

ዓድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ- የደም ትቢያ መቀነትዋ

ከሞት ከባርነት ሥርየት- በደም ለነጻነት ስለት

አበው የተሰውብሽ እ’ ለት

የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ- የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ…

ገጣሚው አለፍ ሲልም በጦርነቱ የዋሉ መሳሪያዎችን፣ የጦር መሪዎችን እጅና ጓንትነት በፈረስ ስሞቻቸው በመቋጠር /ለአብነትም የዳግማዊ ምኒልክ፣ የራስ መኮንን፣ የደጃች ባልቻ ሳፎ፣  የፊታውራሪ ገበየሁና ሌሎችም/ ኢትዮጵያዊያንን ጀግንነትና ወኔ በአጭሩ ቋጥሮታል።

…ድው-እልም ሲል ጋሻዋ- ሲያስተጋባ ከበሮዋ፣

ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ፣

ያባ መቻል ያባ ዳኘው፤ ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው፣

ያባ ጎራው፣ ያባ በለው በለው ሲለው…

ገጣሚ አበረ አያሌው “ፍርድና ዕርድ” በተሰኘው ድንቅ የግጥም ስብስቡ ባሰፈራቸው ስንኞች ‘ነገረ አድዋ’ን ከመንደር ወደ አገር፣ ከአገር ወደ አህጉር በመጨረሻም ከአህጉር አተልቆ ‘ዓለም’ ያደርገዋል፤ አድዋን የአፍሪካ ብርሀን ፈንጣቂ፤ ለእብሪተኞች ደግሞ የትካዜና ቅስም መስበሪያ ምስጢር አድርጓታል። በተለይም ኢትዮጵያ ለገጠማት አሁናዊ የዘር ፖለቲካ አዙሪት አድዋን ለሚያሳንሱ ወገኖች በቅኔው ምላሽ ይሰጣል።

…እነ ምኒልክ ጦር ይዘው ከመድፍ የተዋደቁ

ጎራዴ መዘው የሮጡ በጠብ-መንጃ አፍ ያለቁ

ለጓጉለት ነጻነት -ደማቸውን ያፈሰሱ

ለሰፈር ብቻ አይደለም- የአህጉር ድል አታሳንሱ።

ዓድዋ ሰፈር አይደለም – ዓድዋ መንደር አይደለም እሱ

ዓለም ናት ዓድዋ ቤቱ – ሃገር ናት የድል ትራሱ

ለጠበበ የዘር ቅኔ – የደም ድል አታሳንሱ!

ዶክተር ተሻገር ሽፈራው ‘የነፍስ ርችቶች’ በተሰኘችው የግጥም ስብስብ መፅሃፉ ከቋጠራቸው ስንኞች መካከልም በአድዋ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል የግጥም ውድድር ያሸነፈበት ረጅምና ድንቅ ግጥሙ ነው። በዚህ ረዘም ካለው ግጥም ስንኞች መካከል የአድዋን ምጡቅነት፣ ዝና፣ ነቅዓ ፍትሕ፣ ውበትና ቅኔ በውብ ቃላት የገለጸበት አንጓ ይገኛል።

….

ዓድዋ አንቺ የዝና አጽናፍ

ሕዝቦች እፍ ያሉብሽ ቁጣ – የነበልባል እቶን ጫፍ

እጹብ ክስተት፤ ደቂቅ ረቂቅ፤ ምጡቅ ጠሊቅ

ኬላ ድንበር፣ አድማስ ሰበር፣ የቅርብ ሩቅ

ለትንግርትሽ ብቻ መጥኔ

ትንግርት እውነት፣ ታምር ሁነት፣

የብርቅ ብርቅ፣ የድንቅ ድንቅ

ለሰጠሽው ፍትህ መጠን – ለፍርድሽ ሚዛን ብያኔ

ለንግስትሽ ሥነ ውበት – ለታሪክሽ ምስጢር ቅኔ…

ገጣሚው ይህን የአፍሪካዊያን ሁሉን አቀፍ ድል ለመግለጽ የቀለም፣ የአንደበትና የብራና ወኔ እንዳጣባት ገልጾ፤ ለአድዋ መጮኽና መዘከር እንደሚገባ ያነበንባል።

የታሪክ ፋኖ ዱካው – ሁሉን ችሎ መች ሊያተርፈው

በምን ቀሰም፣ በምን ቀለም – በምን ብዕራና ሊከትበው

……

ሰውአዊ ምስጢራችንን – በምን አቅሙ ሊገልጸው

እኛው ጮኸን – ካልዘከርነው ካልተናገርነው …

በመጨረሻም ይህችን የድል ቁንጮ የማትሞቺ ህያው ጀንበር ሁልጊዜም ተዘመሪ፤ ተወደሽ በሚሉ ስንኞች እንሰነባበት።

… እና ዓድዋ አንቺ በኩር የድል መኸር

የቅኝ ግዛት ቀንበር ሰንሰለቱ እንዲሰበር

ተጠቂዎች አጥናፍ አጥናፍ የመረጡሽ የትግል ዘር

ህይወት ከፍለው እልፍ – ያርጉሽ የመረጡሽ ከአገር አገር

የማታልፊ የማትከስሚ – የማትሞቺ ህያው ጀንበር

ሰብዓዊ ድል ነሽና – ስምሽ ይወደስ ይዘመር…